← Genesis (44/50) → |
1. | ዮሴፍም የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘ። ዓይበታቸው የሚያነሣውን ያህል እህል ሙላላቸው፥ የሁሉንም ብር በየዓይበታቸው አፍ ጨምረው፤ |
2. | በታናሹም ዓይበት አፍ የብሩን ጽዋዬንና የእህሉን ዋጋ ጨምረው። እርሱም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ። |
3. | ነግህ በሆነ ጊዜም ሰዎቹ አህዮቻቸውን ይዘው ይሄዱ ዘንድ ተሰናበቱ። |
4. | ከከተማይቱም ወጥተው ገና ሳይርቁ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ አለ። ተነሥተህ ሰዎቹን ተከተላቸው፤ በደረስህባቸውም ጊዜ እንዲህ በላቸው። በመልካሙ ፋንታ ስለ ምን ክፉን መለሳችሁ? |
5. | ጌታዬ የሚጠጣበት ምሥጢርንም የሚያውቅበት ጽዋ አይደለምን? ባደረጋችሁት ነገር በደላችሁ። |
6. | እርሱም ደርሰባቸው ይህንም ቃል ነገራቸው። |
7. | እነርሱም አሉት። ጌታዬ እንደዚህ ያለውን ቃል ለምን ይናገራል? ባሪያዎችህ ይህን ነገር የሚያደርጉ አይደሉም። |
8. | እነሆ፥ በዓይበታችን አፍ ያገኘነውን ብር ይዘን ከከነዓን አገር ወደ አንተ ተመልሰናል፤ ከጌታህ ቤት ወርቅ ወይስ ብር እንዴት እንሰርቃለን? |
9. | ከባሪያዎችህ ጽዋው የተገኘበት እርሱ ይሙት፤ እኛም ደግሞ ለጌታችን ባሪያዎች እንሁን። |
10. | እርሱም አለ። አሁንም እንዲሁ እንደ ነገራችሁ ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት እርሱ ለእኔ ባሪያ ይሁነኝ፥ እናንተም ንጹሐን ትሆናላችሁ። |
11. | እየራሳቸውም ፈጥነው ዓይበታቸውን ወደ ምድር አወረዱ፥ እየራሳቸውም ዓይበታቸውን ፈቱ። |
12. | እርሱም ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በረበራቸው፥ ጽዋውንም በብንያም ዓይበት ውስጥ አገኘው። |
13. | ልብሳቸውንም ቀደዱ፥ ዓይበታቸውንም በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማይቱ ተመለሱ። |
14. | ይሁዳም ከወንድሞቹ ጋር ወደ ዮሴፍ ገባ፥ እርሱም ገና ከዚያው ነበረ፤ በፊቱም በምድር ላይ ወደቁ። |
15. | ዮሴፍም። ይህ ያደረጋችሁት ነገር ምንድር ነው? እንደ እኔ ያለ ሰው ምሥጢርን እንዲያውቅ አታውቁምን? አላቸው። |
16. | ይሁዳም አለ። ለጌታዬ ምን እንመልሳለን? ምንስ እንናገራለን? ወይስ በምን እንነጻለን? እግዚአብሔር የባሪያዎችህን ኃጢአት ገለጠ፤ እነሆ፥ እኛም ጽዋው ከእርሱ ዘንድ የተገኘበቱም ደግሞ ለጌታዬ ባሪያዎቹ ነን። |
17. | እርሱም እላቸው። ይህን አደርግ ዘንድ አይሆንልኝም፤ ጽዋው የተገኘበቱ ሰው እርሱ ባሪያ ይሁነኝ፤ እናንተም ወደ አባታችሁ በደኅና ውጡ። |
18. | ይሁዳም ወደ እርሱ ቀረበ እንዲህም አለ። ጌታዬ ሆይ፥ እኔ ባርያህ በጌታዬ ጆሮ አንዲት ቃልን እንድናገር እለምናለሁ፤ እኔንም ባሪያህን አትቆጣኝ፤ አንተ እንደ ፈርዖን ነህና። |
19. | ጌታዬ ባሪያዎቹን። አባት አላችሁን ወይስ ወንድም? ብሎ ጠየቀ። |
20. | እኛም ለጌታዬ እንዲህ አልነ። ሸማግሌ አባት አለን፥ በሽምግልናው የወለደውም ታናሽ ብላቴና አለ፤ ወንድሙም ሞተ፥ ከእናቱም እርሱ ብቻውን ቀረ፥ አባቱም ይወድደዋል። |
21. | አንተም ለባሪያዎችህ። ወደ እኔ አምጡት፥ እኔም አየዋለሁ አልህ። |
22. | ጌታዬንም። ብላቴናው አባቱን መተው አይሆንለትም፤ የተወው እንደ ሆነ አባቱ ይሞታልና አልነው። |
23. | ባርያዎችህንም። ታናሽ ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም አልኽን። |
24. | ወደ ባርያህ ወደ አባታችን በተመለስን ጊዜም የጌታዬን ቃል ነገርነው። |
25. | አባታችንም። ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን አለ። |
26. | እኛም አልነው። እንሄድ ዘንድ አይሆንልንም፤ ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ይወርድ እንደ ሆነ እኛም እንወርዳለን፤ ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ከሌለ የዚያን ሰው ፊት ማየት አይቻለንምና። |
27. | ባሪያህ አባቴም እንዲህ አለን። ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆችን እንደ ወለደችልኝ እናንተ ታውቃላችሁ፤ |
28. | አንዱም ከእኔ ወጣ። አውሬ በላው አላችሁኝ፥ እስከ ዛሬም አላየሁትም፤ |
29. | ይህንም ከእኔ ለይታችሁ ደግሞ ብትወስዱት ክፋም ቢያገኘው፥ ሽበቴን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ። |
30. | አሁንም እኔ ወደ አባቴ ወደ ባሪያህ ብሄድ፥ ብላቴናውም ከእኛ ጋር ከሌለ፥ ነፍሱ በብላቴናው ነፍስ ታስራለችና ብላቴናው ከእኛ ጋር እንደሌለ ባየ ጊዜ ይሞታል፤ |
31. | ባሪያዎችህም የባሪያህን የአባታችንን ሽበት በኅዘን ወደ መቃብር ያወርዳሉ። |
32. | እኔ ባሪያህ በአባቴ ዘንድ ስለ ብላቴናው እንዲህ ብዬ ተውሼአለሁና። እርሱንስ ወደ አንተ ባላመጣው በአባቴ ዘንድ በዘመናት ሁሉ ኃጢአተኛ እሆናለሁ። |
33. | ስለዚህም እኔ ባሪያህ በጌታዬ ዘንድ ባሪያ ሆኜ በብላቴናው ፋንታ ልቀመጥ፤ ብላቴናውም ከወንድሞቹ ጋር ይውጣ። |
34. | አለዚያም ብላቴናው ከእኔ ጋር ከሌለ ወደ አባቴ እንዴት እወጣለሁ? አባቴን የሚያገኘውን መከራ እንዳላይ። a |
← Genesis (44/50) → |