← Genesis (42/50) → |
1. | ያዕቆብም በግብፅ እህል እንዳለ ሰማ፥ ያዕቆብም ልጆቹን። ለምን እርስ በርሳችሁ ትተያያላችሁ? አላቸው። |
2. | እንዲህም አለ። እነሆ ስንዴ በግብፅ እንዲገኝ ሰምቼአለሁ፤ ወደዚያ ውረዱ፥ እንድንድንና እንዳንሞትም ከዚያ ሸምቱልን። |
3. | የዮሴፍም አሥሩ ወንድሞቹ ስንዴን ከግብፅ ይሸምቱ ዘንድ ወረዱ፤ |
4. | የዮሴፍን ወንድም ብንያምን ግን ያዕቆብ ከወንድሞቹ ጋር አልሰደደውም። ምናልባት ክፉ እንዳያገኘው ብሎአልና። |
5. | የእስራኤልም ልጆች ለእህል ሸመታ ከመጡቱ ጋር ገቡ፤ በከነዓን አገር ራብ ነበረና። |
6. | ዮሴፍም በምድር ላይ ገዥ ነበረ፥ እርሱም ለምድር ሕዝብ ሁሉ ይሸጥ ነበር፤ የዮሴፍም ወንድሞች በመጡ ጊዜ በምድር ላይ በግምባራቸው ሰገዱለት። |
7. | ዮሴፍም ወንድሞቹን አይቶ አወቃቸው፤ ተለወጠባቸውም፥ ክፉ ቃልንም ተናገራቸው። እናንተ ከወዴት መጣችሁ? አላቸው። እነርሱም። ከከነዓን ምድር እህል ልንሸምት የመጣን ነን አሉት። |
8. | ዮሴፍም ወንድሞቹን አወቃቸው፥ እነርሱ ግን አላወቁትም፤ |
9. | ዮሴፍም ስለ እነርሱ አይቶት የነበረውን ሕልም አሰበ። እንዲህም አላቸው። እናንተ ሰላዮች ናችሁ፤ የምድሩን ዕራቁትነት ልታዩ መጥታችኋል። |
10. | እነርሱም አሉት። ጌታችን ሆይ አይደለም፤ ባሪያዎችህ ስንዴን ሊገዙ መጥተዋል፤ |
11. | እኛ ሁላችን የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ እኛ እውነተኞች ነን፥ ባሪያዎችህስ ሰላዩች አይደሉም። |
12. | እርሱም አላቸው። አይደለም፤ ነገር ግን የአገሩን ዕራቁትነት ልታዩ መጥታችኋል። |
13. | እነርሱም አሉ። ባሪያዎችህ አሥራ ሁለት ወንድማማች በከነዓን ምድር የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ ታናሹም እነሆ ዛሬ ከአባታችን ጋር ነው፥ አንዱም ጠፍቶአል። |
14. | ዮሴፍም አላቸው። እናንተ ሰላዮች ናችሁ ብዬ የተናገርኋችሁ ይህ ነው፤ |
15. | በዚህ ትፈተናላችሁ፤ ታናሽ ወንድማችሁ ካልመጣ በቀር የፈርዖንን ሕይወት ከዚህ አትወጡም። |
16. | እውነትን የምትናገሩ ከሆነ ነገራችሁ ይፈተን ዘንድ ከእናንተ አንዱን ስደዱ፥ ወንድማችሁንም ይዞ ይምጣ እናንተም ታሥራችሁ ተቀመጡ፤ ይህ ካልሆነ የፈርዖንን ሕይወት ሰላዮች ናችሁ። |
17. | ሦስት ቀን ያህል በግዞት ቤት ጨመራቸው። |
18. | በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው። ትድኑ ዘንድ ይህን አድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔርን እፈራለሁና። |
19. | እናንተ የታመናችሁ ከሆናችሁ ከእናንተ አንዱ ወንድማችሁ በግዞታችሁ ቤት ይታሰር እናንተ ግን ሂዱ፥ እህሉንም ለቤታችሁ ራብ ውሰዱ፤ |
20. | ታናሹንም ወንድማችሁን ወደ እኔ ይዛችሁ ኑ፤ ነገራችሁም የታመነ ይሆናልና አትሞቱም። እንዲህም አደረጉ። |
21. | እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ። በእውነት ወንድማችንን በድለናል፥ እኛን በማማጠን ነፍሱ ስትጨነቅ አይተን አልሰማነውምና፤ ስለዚህ ይህ መከራ መጣብን። |
22. | ሮቤልም መልሶ እንዲህ አላቸው። ብላቴናውን አትበድሉ ብያችሁ አልነበረምን? እኔም አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህ እነሆ አሁን ደሙ ይፈላለገናል። |
23. | እነርሱም ዮሴፍ ነገራቸውን እንደሚሰማባቸው አላወቁም፥ በመካከላቸው አስተርጓሚ ነበረና። |
24. | ከእነርሱም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ደግሞም ወደ እነርሱ ተመልሶ ተናገራቸው፥ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ወሰዶ በፊታቸው አሰረው። |
25. | ዮሴፍም ዓይበታቸውን እህል ይሞሉት ዘንድ አዘዘ፤ የእየራሳቸውንም ብር በእየዓይበታቸው ይመልሱት ዘንድ ደግሞም የመንገድ ስንቅ ይሰጡአቸው ዘንድ አዘዘ። እንዲሁም ተደረገላቸው። |
26. | እነርሱም እህሉን በአህዮቻቸው ላይ ጫኑ፥ ከዚያም ተነሥተው ሄዱ። |
27. | ከእነርሱም አንዱ ባደሩበት ስፍራ ለአህያው ገፈራን ይሰጥ ዘንድ ዓይበቱን ሲፈታ ብሩን አየ፥ እነሆም በዓይበቱ አፍ ላይ ነበረች። |
28. | ለወንድሞቹም። ብሬ ተመለሰችልኝ፥ እርስዋም በዓይበቴ አፍ እነኋት አላቸው። ልባቸውም ደነገጠ፥ እየተንቀጠቀጡም እርስ በርሳቸው ተባባሉ። እግዚአብሔር ያደረገብን ይህ ምንድር ነው? |
29. | ወደ አባታቸውም ወደ ያዕቆብ ወደ ከነዓን ምድር መጡ፥ የደረሰባቸውንም ነገር ሁሉ እንዲህ ብለው አወሩ። |
30. | የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው በክፉ ንግግር ተናገረን፥ የምድሪቱም ሰላዮች አስመሰለን። |
31. | እኛም እንዲህ አልነው። እውነተኞች ሰዎች ነን እንጂ ሰላዮች አይደለንም፤ |
32. | እኛ የአባታችን ልጆች አሥራ ሁለት ወንድማማች ነን፤ አንዱ ጠፍቶአል፥ ታናሹም በከነዓን ምድር ዛሬ ከአባታችን ጋር አለ። |
33. | የአገሩም ጌታ ያ ሰው እንዲህ አለን። የታመናችሁ ሰዎች ከሆናችሁ በዚህ አውቃለሁ፤ አንደኛውን ወንድማችሁን ከእኔ ጋር ተዉት፥ ለቤታችሁም ራብ እህልን ወስዳችሁ ሂዱ፤ |
34. | ታናሹንም ወንድማችሁን አምጡልኝ፥ እውነተኞች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁንም በዚህ አውቀዋለሁ፤ ወንድማችሁንም እሰጣችኋለሁ፥ እናንተም በምድሩ ትነግዳላችሁ። |
35. | እንዲህም ሆነ፤ ዓይበታቸውን በፈቱ ጊዜ እነሆ ከእነርሱ እያንዳንዳቸው ብራቸውን በእየዓይበታቸው ተቋጥሮ አገኙት፤ እነርሱም አባታቸውም የብራቸውን ቍጥራት አይተው ፈሩ። |
36. | አባታቸው ያዕቆብም እንዲህ አላቸው። ልጅ አልባ አስቀራችሁኝ፤ ዮሴፍ የለም፥ ስምዖንም የለም፥ ብንያምንም ትወስዱብኛላችሁ፤ ይህ ሁሉ በእኔ ላይ ደረሰ። |
37. | ሮቤልም አባቱን አለው። ወደ አንተ መልሼ ያላመጣሁት እንደ ሆነ ሁለቱን ልጆቼን ግደል፤ እርሱን በእጄ ስጠኝ፥ እኔም ወደ አንተ እመልሰዋለሁ። |
38. | እርሱም አለ። ልጄ ከእናንተ ጋር አይወርድም፤ ወንድሙ ሞቶ እርሱ ብቻ ቀርቶአልና፤ በምትሄዱበት መንገድ ምናልባት ክፉ ነገር ቢያገኘው ሽምግልናዬን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ። a |
← Genesis (42/50) → |