| ← Genesis (39/50) → |
| 1. | ዮሴፍ ግን ወደ ግብፅ ወረደ፤ የፈርዖን ጃንደረባ የዘበኞቹም አለቃ የሚሆን የግብፅ ሰው ጲጥፋራ ወደ ግብፅ ካወረዱት ከእስማኤላውያን እጅ ገዛው። |
| 2. | እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበረ፥ ሥራውም የተከናወነለት ሰው ሆነ፤ በግብፃዊው ጌታውም ቤት ነበረ። |
| 3. | ጌታውም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለ፥ እርሱ የሚሠራውንም ሁሉ እግዚአብሔር በእጁ እንዲያከናውንለት አየ። |
| 4. | ዮሴፍም በጌታው ፊት ሞገስን አገኘ፥ እርሱንም ያገለግለው ነበር፤ በቤቱም ላይ ሾመው፥ ያለውንም ሁሉ በእጁ ሰጠው። |
| 5. | እንዲህም ሆነ፤ በቤቱ ባለውም ሁሉ ላይ ከሾመው በኋላ እግዚአብሔር የግብፃዊውን ቤት ስለ ዮሴፍ ባረከው፤ የእግዚአብሔር በረከት በውጪም በግቢም ባለው ሁሉ ላይ ሆነ። |
| 6. | ያለውንም ሁሉ ለዮሴፍ አስረከበ፤ ከሚበላውም እንጀራ በቀር ምንም የሚያውቀው አልነበረም። የዮሴፍም ፊቱ መልከ መልካምና ውብ ነበረ። |
| 7. | ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይንዋን ጣለች። ከእኔም ጋር ተኛ አለችው። |
| 8. | እርሱም እንቢ አለ፥ ለጌታውም ሚስት እንዲህ አላት። እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የለም፥ ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል፤ |
| 9. | ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለ ሆንሽ ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ? |
| 10. | ይህንም ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ ከእርስዋም ጋር ይሆን ዘንድ አልሰማትም። |
| 11. | እንዲህም ሆነ፤ በዚያን ጊዜ ሥራውን እንዲሠራ፤ ወደ ቤቱ ገባ፤ በቤትም ውስጥ ከቤት ሰዎች ማንም አልነበረም። |
| 12. | ከእኔ ጋር ተኛ ስትል ልብሱን ተጠማጥማ ያዘች፤ እርሱም ልብሱን በእጅዋ ትቶላት ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ። |
| 13. | እንዲህም ሆነ፤ ልብሱን ትቶ ወደ ውጭ እንደ ሸሸ ባየች ጊዜ፥ |
| 14. | የቤትዋን ሰዎች ወደ እርስዋ ጠርታ እንዲህ ብላ ነገረቻቸው። እዩ፤ ዕብራዊው ሰው በእኛ እንዲሣለቅ አግብቶብናል፤፤ እርሱ ከእኔ ጋር ሊተኛ ወደ እኔ ገባ፥ እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ ጮኽሁ፤ |
| 15. | ድምፄንም ከፍ አድርጌ እንደ ጮኽሁ ቢሰማ ልብሱን በእኔ ዘንድ ጥሎ ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ። |
| 16. | ጌታው ወደ ቤቱ እስኪገባ ድረስም ልብሱን ከእርስዋ ዘንድ አኖረች። |
| 17. | ይህንም ነገር እንዲህ ብላ ነገረችው። ያገባህልን ዕብራዊው ባሪያ ሊሣለቅብኝ ወደ እኔ ገባ፤ |
| 18. | እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ልብሱን በእጄ ተወና ወደ ውጭ ሸሸ። |
| 19. | ጌታውም። ባሪያህ እንዲህ አደረገኝ ብላ የነገረችውን የሚስቱን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ። |
| 20. | የዮሴፍም ጌታ ወሰደው፥ የንጉሡ እስረኞችም ወደሚታሰሩበት ስፍራ ወደ ግዞት ቤት አገባው፤ ከዚያም በግዞት ነበረ። |
| 21. | እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ ምሕረትንም አበዛለት፥ በግዞት ቤቱም አለቃ ፊት ሞገስን ሰጠው። |
| 22. | የግዞት ቤቱም አለቃ በግዞት ያሉትን እስረኞች ሁሉ በዮሴፍ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዚያም የሚደረገው ነገር ሁሉ እርሱ የሚያደርገው ነበረ። |
| 23. | የግዞት ቤቱም አለቃ በእጁ ያለውን ነገር ከቶ አላሰበም፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ የሚያደርገውንም ሁሉ እግዚአብሔር ያቀናለት ነበር። |
| ← Genesis (39/50) → |