| ← Genesis (38/50) → |
| 1. | በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ወረደ፥ ስሙን ኤራስ ወደሚሉት ወደ ዓዶሎማዊውም ሰው ገባ። |
| 2. | ከዚያም ይሁዳ የከነዓናዊውን የሴዋን ሴት ልጅ አየ፤ ወሰዳትም፥ ወደ እርስዋም ገባ። |
| 3. | ፀነሰችም ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም ዔር ብላ ጠራችው። |
| 4. | ደግሞም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም አውናን ብላ ጠራችው። |
| 5. | እንደ ገና ደግሞ ወንድ ልጅን ወለደች፥ ስሙንም ሴሎም ብላ ጠራችው፤ እርሱንም በወለደች ጊዜ ክዚብ በሚባል አገር ነበረች። |
| 6. | ይሁዳም ለበኵር ልጁ ለዔር ትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው። |
| 7. | የይሁዳም የበኵር ልጅ ዔር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው። |
| 8. | ይሁዳም አውናን። ወደ ወንድምህ ሚስት ግባ፥ አግባትም፥ ለወንድምህም ዘርን አቁምለት አለው። |
| 9. | አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን አወቀ፤ ወደ ወንድሙ ሚስት በገባ ጊዜ ለወንድሙ ዘር እንዳይሰጥ ዘሩን በምድር ያፈስስው ነበር። |
| 10. | ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ሆነበት፥ እርሱንም ደግሞ ቀሠፈው። |
| 11. | ይሁዳም ምራቱን ትዕማርን። ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ተቀመጪ አላት፤ እርሱ ደግሞ እንደ ወንድሞቹ እንዳይሞት ብሎአልና። ትዕማርም ሄዳ በአባትዋ ቤት ተቀመጠች። |
| 12. | ከብዙ ዘመንም በኋላ የይሁዳ ሚስት የሴዋ ልጅ ሞተች፤ ይሁዳም ተጽናና፥ የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱት ሰዎችም ወደ ተምና ወጣ፥ እርሱም ዓዶሎማዊው ወዳጁም ኤራስ። |
| 13. | ለትዕማርም። እነሆ አማትሽ ይሁዳ የበጎቹን ጠጕር ይሸልት ዘንድ ወደ ተምና ይወጣል ብለው ነገሩአት። |
| 14. | እርስዋም የመበለትነትዋን ልብስ አወለቀች፥ መጎናጸፊያዋንም ወሰደች፥ ተሸፈነችም፥ ወደ ተምናም በሚወስደው መንገድ ዳር በኤናይም ደጅ ተቀመጠች፤ ሴሎም እንደ አደገ ሚስትም እንዳልሆነችው አይታለችና። |
| 15. | ይሁዳም ባያት ጊዜ ጋለሞታን መሰለችው፤ ፊትዋን ተሸፍና ነበርና። |
| 16. | ወደ እርስዋም አዘነበለ። እባክሽ ወደ አንቺ ልግባ አላት፤ እርስዋ ምራቱ እንደ ሆነች አላወቀም ነበርና። እርስዋም። ወደኔ ብትገባ ምን ትሰጠኛለህ? አለችው። |
| 17. | የፍየል ጠቦት ከመንጋዬ እሰድድልሻለሁ አላት። እርስዋም። እስክትሰድድልኝ ድረስ መያዣ ትሰጠኛለህን? አለችው። |
| 18. | እርሱም። ምን መያዣ ልስጥሽ? አላት። እርስዋም። ቀለበትህን፥ አምባርህን፥ በእጅህ ያለውን በትር አለች። እርሱም ሰጣትና ከእርስዋ ጋር ደረሰ፥ እርስዋም ፀነሰችለት። |
| 19. | እርስዋም ተነሥታ ሄደች፥ መጎናጸፊያዋንም አውልቃ የመበለትነትዋን ልብስ ለበሰች። |
| 20. | ይሁዳም መያዣውን ከሴቲቱ እጅ ይቀበል ዘንድ በወዳጁ በዓዶሎማዊው እጅ የፍየሉን ጠቦት ላከላት፤ እርስዋንም አላገኛትም። |
| 21. | እርሱም የአገሩን ሰዎች። በኤናይም በመንገድ ዳር ተቀምጣ የነበረች ጋለሞታ ወዴት ናት? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም። በዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉት። |
| 22. | ወደ ይሁዳም ተመልሶ እንዲህ አለው። አላገኘኋትም፤ የአገሩም ሰዎች ደግሞ። ከዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉኝ። |
| 23. | ይሁዳም። እኛ መዘበቻ እንዳንሆን ትውሰደው፤ እነሆ የፍየሉን ጠቦት ሰደድሁላት፥ አንተም አላገኘሃትም አለ። |
| 24. | እንዲህም ሆነ፤ ከሦስት ወር በኋላ ለይሁዳ። ምራትህ ትዕማር ሴሰነች፤ ደግሞም በዝሙት እነሆ ፀነሰች ብለው ነገሩት። ይሁዳም። አውጡአትና በእሳት ትቃጠል አለ። |
| 25. | እርስዋም ባወጡአት ጊዜ ወደ አማትዋ እንዲህ ብላ ላከች። ለዚህ ለባለ ገንዘብ ነው የፀነስሁት፤ ተመልከት፤ ይህ ቀለበት፥ ይህ አምባር፥ ይህ በትር የማን ነው? |
| 26. | ይሁዳም አወቀ። ከእኔ ይልቅ እርስዋ እውነተኛ ሆነች፤ ልጄን ሴሎምን አልሰጠኋትምና አለ። ደግሞም አላወቃትም። |
| 27. | በመውለጃዋም ጊዜ እነሆ መንታ ልጆች በሆድዋ ነበሩ። |
| 28. | ስትወልድም አንዱ እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም ቀይ ፈትል ወስዳ በእጁ አሰረች። ይህ መጀመሪያ ይወጣል አለች። |
| 29. | እንዲህም ሆነ፤ እጁን በመለሰ ጊዜ እነሆ ወንድሙ ወጣ፤ እርስዋም። ለምን ጥስህ ወጣህ? አለች፤ ስሙንም ፋሬስ ብላ ጠራችው። |
| 30. | ከእርሱም በኋላ ቀይ ፈትል በእጁ ያለበት ወንድሙ ወጣ፤ ስሙም ዛራ ተባለ። a |
| ← Genesis (38/50) → |