← Genesis (37/50) → |
1. | ያዕቆብም አባቱ በስደት በኖረበት አገር በከነዓን ምድር ተቀመጠ። |
2. | የያዕቆብም ትውልድ ይህ ነው። ዮሴፍ የአሥራ ሰባት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ ከወንድሞቹ ጋር በጎችን ይጠብቅ ነበር፤ እርሱም ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዘለፋ ልጆች ጋር ሳለ ብላቴና ነበረ፤ ዮሴፍም የክፋታቸውን ወሬ ወደ አባታቸው አመጣ። |
3. | እስራኤልም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወደው ነበር፥ እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበርና፤ በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት ። |
4. | ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንዲወደው ባዩ ጊዜ ጠሉት፥ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም። |
5. | ዮሴፍም ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ እነርሱም እንደ ገና በብዙ ጠሉት። |
6. | እርሱም አላቸው። እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፤ |
7. | እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበርና፥ እነሆም፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከብበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ። |
8. | ወንድሞቹም። በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ልትገዛ ይሆን? አሉት። እንደ ገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ ይልቁን ጠሉት። |
9. | ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እንዲህም አለ። እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፤ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ። |
10. | ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ አባቱም ገሠጸው፥ እንዲህም አለው። ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድር ነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን? |
11. | ወንድሞቹም ቀኑበት አባቱ ግን ነገሩን ይጠብቀው ነበር። |
12. | ወንድሞቹ በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ። |
13. | እስራኤልም ዮሴፍን። ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን የሚጠብቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እልክህ ዘንድ ና አለው። እርሱም። እነሆኝ አለው ። |
14. | እርሱም። ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ አለው። እንዲህም ከኬብሮን ቈላ ሰደደው፥ ወደ ሴኬምም መጣ። |
15. | እነሆም በምድረ በዳ ሲቅበዘበዝ ሳለ አንድ ሰው አገኘው፤ ሰውዮውም። ምን ትፈልጋለህ? ብሎ ጠየቀው። |
16. | እርሱም ወንድሞቼን እፈልጋለሁ፤ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ አለ። |
17. | ሰውዮውም። ከዚህ ተነሥተዋል፤ ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ሰምቼአቸዋለሁ አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ፥ በዶታይንም አገኛቸው። |
18. | እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩት፥ ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። |
19. | አንዱም ለአንዱ እንዲህ አለው። ያ ባለ ሕልም ይኸው መጣ። |
20. | አሁንም ኑ፥ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው። ክፉ አውሬም በላው እንላለን፤ ከሕልሞቹም የሚሆነውን እናያለን። |
21. | ሮቤልም ይህን ሰማ፥ ከእጃቸውም አዳነው፥ እንዲህም አለ። ሕይወቱን አናጥፋ። |
22. | ሮቤል። ደም አታፍስሱ፤ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት፥ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት አላቸው። እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። |
23. | እንዲህም ሆነ፤ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱን ቀሚሱን ገፈፉት፤ |
24. | ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ። |
25. | እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ፤ ዓይናቸውንም አንሥተው አዩ፥ እነሆም የእስማኤላውያን ነገዶች ወደ ግብፅ ለመውረድ ከገለዓድ መጡ፤ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን ከርቤም ተጭነው ነበር። |
26. | ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው። ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድር ነው? |
27. | ኑ፥ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፥ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና። ወንድሞቹም የእርሱን ነገር ሰሙት። |
28. | የምድያም ነጋዶችም አለፉ፤ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጕድጓድ አወጡት፤ ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሀያ ብር ሸጡት፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት። |
29. | ሮቤልም ወደ ጕድጓዱ ተመለሰ፥ እነሆም ዮሴፍ በጕድጓድ የለም፤ ልብሱንም ቀደደ። |
30. | ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ። ብላቴናው የለም፤ እንግዲህ እኔ ወዴት እሄዳለሁ? አለ። |
31. | የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ፥ የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት። |
32. | ብዙ ኅብር ያለበትን ቀሚሱንም ላኩ፥ ወደ አባታቸውም አገቡት፥ እንዲህም አሉት። ይህንን አገኘነ፤ ይህ የልጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እስኪ እየው። |
33. | እርሱም አውቆ። የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍ በእርግጥ ተበጫጭቋል አለ። |
34. | ያዕቆብም ልብሱን ቀደደ፥ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። |
35. | ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፤ መጽናናትን እንቢ አለ፥ እንዲህም አለ። ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ። አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ። |
36. | እነዚያ የምድያም ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብፅ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጲጥፋራ ሸጡት። |
← Genesis (37/50) → |