| ← Genesis (34/50) → |
| 1. | ለያዕቆብ የወለደችለት የልያ ልጅ ዲናም የዚያን አገር ሴቶች ልጆችን ለማየት ወጣች። |
| 2. | የአገሩ አለቃ የኤዊያዊ ሰው የኤሞር ልጅ ሴኬም አያት፤ ወሰዳትም ከእርስዋም ጋር ተኛ፥ አስነወራትም። |
| 3. | ልቡናውም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈ፥ ብላቴናይቱንም ወደዳት፥ ልብዋንም ደስ በሚያሰኛት ነገር ተናገራት። |
| 4. | ሴኬምም አባቱን ኤሞርን። ይህችን ብላቴና አጋባኝ ብሎ ነገረው። |
| 5. | ያዕቆብም ልጁን ዲናን እንዳስነወራት ሰማ፤ ልጆቹም ከከብቶቻቸው ጋር በምድረ በዳ ነበሩ፤ ያዕቆብም እስኪመጡ ድረስ ዝም አለ። |
| 6. | የሴኬም አባት ኤሞርም ይነግረው ዘንድ ወደ ያዕቆብ ወጣ። |
| 7. | የያዕቆብም ልጆች ይህንን በሰሙ ጊዜ ከምድረ በዳ መጡ፤ የያዕቆብን ልጅ በመተኛቱ በእስራኤል ላይ ስንፍናን ስላደረገ አዘኑ፥ እጅግም ተቈጡ፤ እንዲህ አይደረግምና። |
| 8. | ኤሞርም እንዲህ ብሎ ነገራቸው። ልጄ ሴኬም በልጃችሁ ፍቅር ልቡ ተነድፎአልና ሚስት እንድትሆነው እባካችሁ እርስዋን ስጡት። |
| 9. | ጋብቾችም ሁኑን፤ ሴቶች ልጆቻችሁን ስጡን፥ እናንተም የእኛን ሴቶች ልጆች ውሰዱ። |
| 10. | ከእኛም ጋር ተቀመጡ፥ ምድሪቱም በፊታችሁ ናት፤ ኑሩባት፥ ነግዱም፥ ግዙአትም። |
| 11. | ሴኬምም አባትዋንና ወንድሞችዋን እንዲህ አለ። በፊታችሁ ሞገስን ባገኝ የምትሉኝን እሰጣለሁ። |
| 12. | ብዙ ማጫና እጅ መንሻ አምጣ በሉኝ፥ በነገራችሁኝም መጠን እሰጣለሁ፤ ይህችን ብላቴና ግን አጋቡኝ። |
| 13. | የያዕቆብም ልጆች ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መለሱ፥ እኅታቸውን ዲናን አርክሶአታልና፤ |
| 14. | እንዲህም አሉአቸው። እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ለመስጠት ይህንን ነገር እናደርግ ዘንድ አይቻለንም፤ ይህ ነውር ይሆንብናልና። |
| 15. | እንደ እኛ ሆናችሁ ወንዶቻችሁን ሁሉ ብትገርዙ በዚህ ብቻ እሺ እንላችኋለን፤ |
| 16. | ሴቶች ልጆቻችንን እንሰጣችኋለን፥ የእናንተንም ሴቶች ልጆች እንወስዳለን፤ አንድ ሕዝብም ሆነን ከእናንተ ጋር እንኖራለን። |
| 17. | ትገረዙ ዘንድ እኛን ባትሰሙ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን። |
| 18. | ነገራቸውም በኤሞር ልጅ በሴኬምና በኤሞር ዘንድ የተወደደ ሆነ። |
| 19. | ብላቴናውም ያሉትን ያደርግ ዘንድ አልዘገየም፥ የያዕቆብን ልጅ ወድዶአልና፤ እርሱም በአባቱ ቤት ካሉት ሁሉ የከበረ ነበረ። |
| 20. | ኤሞርና ሴኬም ልጁም ወደ ከተማቸው አደባባይ ገቡ፥ ለከተማቸውም ሰዎች እንዲህ ብለው ነገሩ። |
| 21. | እነዚህ ሰዎች በእኛ ዘንድ የሰላም ሰዎች ናቸው፤ በምድራችን ይቀመጡ፥ ይነግዱባትም፥ እነሆም ምድሪቱ ሰፊ ናት፤ ሴቶች ልጆቻቸውን እንውሰድ፥ ለእነርሱም ሴቶች ልጆቻችንን እንስጥ። |
| 22. | ነገር ግን አንድ ሕዝብ ሆነን ከእኛ ጋር ይቀመጡ ዘንድ በዚህ ነገር ብቻ እሺ ይሉናል፤ እነርሱ እንደ ተገረዙ ወንዶቻችንን ሁሉ ብንገርዝ። |
| 23. | ከብቶቻቸውም ያላቸውም ሁሉ እንስሶቻቸውም ሁሉ ለእኛ አይደሉምን? በዚህ ነገር ብቻ እሺ ያልናቸው እንደ ሆነ ከእኛ ጋር ይቀመጣሉ። |
| 24. | ከከተማይቱም አደባባይ የሚወጡ ሁሉ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን እሺ አሉ፤ ከከተማይቱ አደባባይ የሚወጡት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ። |
| 25. | ሦስተኛም ቀን በሆነ ጊዜ እጅግ ቆስለው ሳሉ፥ የዲና ወንድሞች የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ እየራሳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ሳይፈሩ ወደ ከተማ ገቡ፥ ወንዱንም ሁሉ ገደሉ፤ |
| 26. | ኤሞርንና ልጁን ሴኬምንም በሰይፍ ገደሉ፥ እኅታቸውን ዲናንም ከሴኬም ቤት ይዘው ወጡ። |
| 27. | የያዕቆብም ልጆች እኅታቸውን ዲናን ሰለ አረከሱአት ወደ ሞቱት ገብተው ከተማይቱን ዘረፉ፤ |
| 28. | በጎቻቸውንም ላሞቻቸውንም አህዮቻቸውንም በውጭም በከተማም ያለውን ወሰዱ። |
| 29. | ሀብታቸውን ሁሉ ሕፃናቶቻቸውንና ሴቶቻቸውንም ሁሉ ማረኩ፥ በቤት ያለውንም ሁሉ ዘረፉ። |
| 30. | ያዕቆብም ሌዊንና ስሞዖንን እንዲህ አለ። በዚች አገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፤ እኔ በቍጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል፤ እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ። |
| 31. | እነርሱም። በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ያደርግባትን? አሉ። a |
| ← Genesis (34/50) → |