← Genesis (33/50) → |
1. | ያዕቆብም ዓይኑን አነሣ፥ እነሆም ዔሳውን ሲመጣ አየው፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች ነበሩ፤ ልጆቹንም ከፍሎ ወደ ልያና ወደ ራሔል ወደ ሁለቱም ባሪያዎች አደረጋቸው፤ |
2. | ባሪያዎችንና ልጆቻቸውንም በፊት አደረገ፥ ልያንና ልጆችዋንም በኋለኛው ስፍራ፥ ራሔልንና ዮሴፍንም ከሁሉ በኋላ አደረገ። |
3. | እርሱም በፊታቸው አለፈ፤ ወደ ወንድሙም እስኪደርስ ድረስ ወደ ምድር ሰባት ጊዜ ሰገደ። |
4. | ዔሳውም ሊገናኘው ሮጠ፥ አንገቱንም አቅፎ ሳመው፤ ተላቀሱም። |
5. | ዓይኑንም አነሣና ሴቶችንና ልጆችን አየ፥ እንዲህም አለ። እነዚህ ምኖችህ ናቸው? እርሱም። እግዚአብሔር ለእኔ ለባሪያህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው አለ። |
6. | ሴቶች ባሪያዎችም ከልጆቻቸው ጋር ቀርበው ሰገዱ፤ |
7. | ደግሞም ልያና ልጆችዋ ቀርበው ሰገዱ፤ ከዚያም በኋላ ዮሴፍና ራሔል ቀርበው ሰገዱ። |
8. | እርሱም። ያገኘሁት ይህ ሠራዊት ሁሉ ምንህ ነው? አለ። እርሱም። በጌታዬ ፊት ሞገስን አገኝ ዘንድ ነው አለ። |
9. | ዔሳውም። ለእኔ ብዙ አለኝ፤ ወንድሜ ሆይ፥ የአንተ ለአንተ ይሁን አለ። |
10. | ያዕቆብም አለ። እንደዚህ አይደለም፤ ነገር ግን በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ እጅ መንሻዬን ተቀበለኝ፤ የእግዚአብሔርን ፊት እንደሚያይ ፊትህን አይቼአለሁና፥ በቸርነትም ተቀብለኸኛልና። |
11. | ይህችንም ያመጣሁልህን በረከቴን ተቀበል፤ እግዚአብሔር በቸርነት ሰጥቶኛልና፥ ለእኔም ብዙ አለኝና። እስኪቀበለውም ድረስ ዘበዘበው። |
12. | እርሱም። ተነሣና እንሂድ፥ እኔም በፊትህ እሄዳለሁ አለ። |
13. | እርሱም አለው። ጌታዬ ሆይ፥ ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ በጎችና ላሞችም ግልገሎቻቸውን ያጠባሉ፤ ሰዎችም አንድ ቀን በችኮላ የነዱአቸው እንደ ሆነ ከብቶቹ ሁሉ ይሞታሉ። |
14. | ጌታዬ ከባሪያው ፊት ቀድሞ ይለፍ፤ እኔም ወደ ሴይር ከጌታዬ ዘንድ እስክደርስ ድረስ ከፊቴ ባሉት በእንስሳቱ እርምጃና በሕፃናቱ እርምጃ መጠን በዝግታ እከተላለሁ። |
15. | ዔሳውም። ከእኔ ጋር ካሉት ሰዎች ከፍዬ ልተውልህን? አለ። እርሱም። ይህ ለምንድር ነው? በጌታዬ ዘንድ ሞገስን ማግኘት ይበቃኛል አለ። |
16. | ዔሳውም በዚያን ቀን ወደ ሴይር መንገዱን ተመለሰ። |
17. | ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት ሄደ፤ በዚያም ለእርሱ ቤትን ሠራ፥ ለከብቶችም ዳሶችን አደረገ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም ሱኮት ብሎ ጠራው። |
18. | ያዕቆብም ከሁለት ወንዞች መካከል በተመለሰ ጊዜ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሴኬም ከተማ በደኅንነት መጣ፤ በከተማይቱም ፊት ሰፈረ። |
19. | ድንኳኑን ተክሎበት የነበረውንም የእርሻውን ክፍል ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ በጎች ገዛው። |
20. | በዚያም መሠውያውን አቆመ፥ ያንም ኤል ኤሎሄ እስራኤል ብሎ ጠራው። |
← Genesis (33/50) → |