← Genesis (31/50) → |
1. | ያዕቆብም የላባ ልጆች ያሉትን ነገር። ያዕቆብ ለአባታችን የሆነውን ሁሉ ወሰደ፤ ይህንም ሁሉ ክብር ከአባታችን ከብት አገኘ ሲሉ ሰማ። |
2. | ያዕቆብም የላባን ፊት አየ፥ እነሆም ከእርሱ ጋር እንደ ዱሮው አልሆነም። |
3. | እግዚአብሔርም ያዕቆብን። ወደ አባትህ ምድር ወደ ዘመዶችህም ተመለስ፤ ከአንተም ጋር እሆናለሁ አለው። |
4. | ያዕቆብም ልኮ ራሔልንና ልያን ወደ በጎቹ ስፍራ ወደ ሜዳ ጠራቸው፥ |
5. | እንዲህም አላቸው። የአባታችሁ ፊት ከእኔ ጋር እንደ ዱሮ እንዳልሆነ አያለሁ፤ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር ነው። |
6. | እኔ ባለኝ ጕልበቴ ሁሉ አባታችሁን እንዳገለገልሁ ታውቃላችሁ። |
7. | አባታችሁ ግን አታለለኝ፥ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለወጠ፤ እግዚአብሔር ግን ክፉ ያደርግብኝ ዘንድ አልፈቀደለትም። |
8. | ደመወዝህ ዝንጕርጕሮች ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ዝንጕርጕሮችን ወለዱ፤ ሽመልመሌ መሳዮቹ ደመወዝህ ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መሳዮችን ወለዱ። |
9. | እግዚአብሔርም የአባታችሁን በጎች ሁሉ ነሥቶ ለእኔ ሰጠኝ። |
10. | እንዲህም ሆነ፤ በጎቹ በጎመጁ ጊዜ ዓይኔን አንሥቼ በሕልም አየሁ፤ እነሆም፥ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ነበሩ። |
11. | የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም። ያዕቆብ ሆይ አለኝ፤ እኔም። እነሆኝ አልሁት። |
12. | እንዲህም አለኝ። ዓይንህን አቅንተህ እይ፤ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ናቸው፤ ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና። |
13. | ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፤ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ አገር ውጣ፥ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ። |
14. | ራሔልና ልያም መልሰው እንዲህ አሉት። በአባታችን ቤት ለእኛ ድርሻና ርስት በውኑ ቀርቶልናልን? |
15. | እኛ በእርሱ ዘንድ እንደ ባዕድ የተቈጠርን አይደለንምን? እርሱ እኛን ሸጦ ዋጋችንን በልቶአልና። |
16. | ስለዚህም እግዚአብሔር ከአባታችን የነሣው ይህ ሁሉ ሀብት ለእኛና ለልጆቻችን ነው፤ አሁንም እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ አድርግ። |
17. | ያዕቆብም ተነሣ፥ ልጆቹንና ሚስቶቹንም በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤ |
18. | መንጎቹንም ሁሉ፥ የቤቱንም ዕቃ ሁሉ፥ በሁለት ወንዞች መካከል ሳለ ያገኛቸውን ከብቶች ሁሉ ይዞ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ ከነዓን ምድር ሄደ። |
19. | ላባ ግን በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር፤ ራሔልም የአባትዋን ተራፊም ሰረቀች። |
20. | ያዕቆብም የሶርያውን ሰው ላባን ከድቶ ኮበለለ፥ መኮብለሉንም፥ አልነገረውም። |
21. | እርሱም ያለውን ሁሉ ይዞ ኮበለለ፤ ተነሥቶም ወንዙን ተሻገረ፥ ፊቱንም ወደ ገለዓድ ተራራ አቀና። |
22. | በሦስተኛውም ቀን የያዕቆብ መኮብለል ለላባ ተነገረው። |
23. | ከወንድሞቹም ጋር ሆኖ የሰባት ቀን መንገድ ያህል ተከተለው፥ በገለዓድ ተራራም ላይ ደረሰበት። |
24. | እግዚአብሔርም ወደ ሶርያው ሰው ወደ ላባ በሌሊት ሕልም መጥቶ። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ አለው። |
25. | ላባም ደረሰበት፤ ያዕቆብም ድንኳኑን በተራራው ተክሎ ነበር፤ ላባም ከወንድሞቹ ጋር በገለዓድ ተራራ ድንኳኑን ተከለ። |
26. | ላባም ያዕቆብን አለው። ለምን እንዲህ አደረግህ? ከእኔ ከድተህ ኮበለልህ፥ ልጆቼንም በሰይፍ እንደ ተማረኩ ዓይነት ነዳሃቸው። |
27. | ስለምን በስውር ሸሸህ? ከእኔም ከድተህ ስለምን ኮበለልህ? በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና እንድሰድድህ ለምን አልነገርኸኝም? |
28. | ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆቼን እንድስም ስለ ምን አልፈቀድህልኝም? ይህንም በስንፍና አደረግህ። |
29. | ክፉ አደርግባችሁ ዘንድ ኃይል ነበረኝ፤ ነገር ግን የአባታችሁ አምላክ ትናንት። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ ብሎ ነገረኝ። |
30. | አሁንም የአባትህን ቤት ከናፈቅህ ሂድ፤ ነገር ግን አምላኮቼን ለምን ሰረቅህ? |
31. | ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው። ልጆችህን ከእኔ የምትቀማኝ ስለመሰለኝና ስለፈራሁ ይህን አደረግሁ። |
32. | አምላኮችህን የምታገኝበት ሰው ግን እርሱ ይሙት፤ የአንተ የሆነውም በእኔ ዘንድ ይገኝ እንደ ሆነ በወንድሞቻችን ፊት ፈልግ፥ ለአንተም ውሰደው አለ። ራሔል እንደ ሰረቀቻቸው ያዕቆብ አያውቅም ነበርና። |
33. | ላባም ወደ ያዕቆብ ድንኳንና ወደ ልያ ድንኳን ወደ ሁለቱም ባሪያዎች ድንኳን ገባ፥ ነገር ግን አላገኘም። ከልያም ድንኳን ወጥቶ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ። |
34. | ራሔልም ተራፊምን ወስዳ ከግመል ኮርቻ በታች ሸሸገች፥ በላዩም ተቀመጠችበት። ላባም ድንኳኑን ሁሉ ፈለገ፥ አንዳችም አላገኘም። |
35. | እርስዋም አባትዋን። በፊትህ ለመቆም ስላልቻልሁ አትቆጣብኝ፤ በሴቶች የሚደርስ ግዳጅ ደርሶብኛልና አለችው። እርሱም ፈለገ፥ ነገር ግን ተራፊምን አላገኘም። |
36. | ያዕቆብም ተቆጣ ላባንም ወቀሰው፤ ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው። የበደልሁህ በደል ምንድር ነው? ኃጢአቴስ ምንድር ነው ይህን ያህል ያሳደድኸኝ? |
37. | አሁንም ዕቃዬን ሁሉ በረበርህ፤ ከቤትህስ ዕቃ ሁሉ ምን አገኘህ? እነርሱ በእኛ በሁለታችን መካከል ይፈርዱ ዘንድ በወንድሞቼና በወንድሞችህ ፊት አቅርበው። |
38. | ሀያ ዓመት ሙሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ በጎችህና ፍየሎችህ አልጨነገፉም፤ የመንጎችህንም ጠቦቶች አልበላሁም፤ አውሬ የሰበረውን አላመጣሁልህም ነበር፤ |
39. | እኔ ስለ እርሱ እከፍልህ ነበርሁ፤ በቀንም በሌሊትም የተሰረቀውን ከእጄ ትሻው ነበርህ። |
40. | የቀን ሐሩር የሌሊት ቍር ይበላኝ ነበር፥ እንቅልፍም ከዓይኔ ጠፋ። |
41. | እንዲሁ በአንተ ቤት ሀያ ዓመት ነበርሁ አሥራ አራት ዓመት ስለ ሁለቱ ሴቶች ልጆችህ፥ ስድስት ዓመትም ስለ በጎችህ ተገዛሁልህ፤ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለዋወጥኸው። |
42. | የአባቴ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም ፍርሃት ከእኔ ጋር ባይሆንስ ዛሬ ባዶ እጄን በሰደድኸኝ ነበር፤ እግዚአብሔር መከራዬንና የእጆቼን ድካም አየ፥ ትናንትም ገሠጸህ። |
43. | ላባም እንዲህ ብሎ ለያቆብ መለሰለት። ሴቶቹ ልጆች ልጆቼ ናቸው፥ ሕፃናቱም ሕፃናቴ ናቸው፥ መንጎቹም መንጎቼ ናቸው፥ የምታየውም ሁሉ የእኔ ነው፤ ዛሬም በእነዚህ በሴቶች ልጆቼና በወለዱአቸው ልጆቻቸው ላይ ምን ላደርግ ይቻላል? |
44. | አሁንም ና፥ አንተና እኔ ቃል ኪዳን እንጋባ፤ በእኔና በአንተ መካከልም ምስክር ይሁን። |
45. | ያዕቆብም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አቆመ። |
46. | ያዕቆብም ወንድሞቹን። ድንጋይ ሰብስቡ አላቸው፤ እነርሱም ድንጋይ ሰብስበው ከመሩ፤ በድንጋዩም ክምር ላይ በሉ። |
47. | ላባም ይጋር ሠሀዱታ ብሎ ጠራት፤ ያዕቆብም ገለዓድ አላት። |
48. | ላባም። ይህች ክምር በእኔና በአንተ መካከል ዛሬ ምስክር ናት አለ። ስለዚህም ስምዋ ገለዓድ ተባለ፤ |
49. | ደግሞም ምጽጳ ተባለ። እኛ በተለያየን ጊዜ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ሆኖ ይጠብቅ ብሎአልና። |
50. | ልጆቼን ብትበድላቸው ወይም በላያቸው ሚስቶችን ብታገባባቸው ከእኛ ጋር ያለ ሰው የለም፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ምስክር ነው። |
51. | ላባም ያዕቆብን አለው። በእኔና በአንተ መካከል እነሆ ይህች ክምር፥ እነሆም ያቆምኋት ሐውልት፤ |
52. | እኔ ወደ አንተ ይህችን ክምር እንዳላልፍ፥ አንተም ለክፋት ወደ እኔ ይህችን ክምርና ይህችን ሐውልት እንዳታልፋት፥ ይህች ክምር ምስክር ናት፥ ይህችም ሐውልት ምስክር ናት። |
53. | የአብርሃም አምላክ የናኮርም አምላክ የአባታቸውም አምላክ በእኛ መካከል ይፍረድ። ያዕቆብም በአባቱ በይስሐቅ ፍርሃት ማለ። |
54. | ያዕቆብም በተራራው ላይ መሥዋዕትን ሠዋ፥ ወንድሞቹንም እንጀራ እንዲበሉ ጠራ፤ እነርሱም እንጀራን በሉ፥ በዚያም በተራራ አደሩ። |
55. | ላባም ማልዶ ተነሥቶ ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆቹን ሳመ ባረካቸውም፤ ላባም ተመልሶ ወደ ስፍራው ሄደ። |
← Genesis (31/50) → |