← Genesis (30/50) → |
1. | ራሔልም ለያዕቆብ ልጆችን እንዳልወለደች ባየች ጊዜ በእኅትዋ ቀናችባት፤ ያቆብንም። ልጅ ስጠኝ፤ ይህስ ካልሆነ እሞታለሁ አለችው። |
2. | ያዕቆብም ራሔልን ተቆጥቶ። በውኑ እኔ የሆድን ፍሬ በነሣሽ በእግዚአብሔር ቦታ ነኝን? አላት። |
3. | እርስዋም ባሪያዬ ባላ እነሆ አለች፤ ድረስባት፤ በእኔም ጭን ላይ ትውለድ፥ የእርስዋም ልጆች ለእኔ ደግሞ ይሁኑልኝ አለች። |
4. | ባሪያዋን ባላንም ሚስት ትሆነው ዘንድ ለእርሱ ሰጠችው፤ ያዕቆብም ደረሰባት። |
5. | ባላም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደችለት። |
6. | ራሔልም። እግዚአብሔር ፈረደልኝ፥ ቃሌንም ደግሞ ሰማ፥ ወንድ ልጅንም ሰጠኝ አለች፤ ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ ጠራችው። |
7. | የራሔልም ባሪያ ባላ ደግማ ፀነሰች፥ ለያዕቆብም ሁለተኛ ወንድ ልጅን ወለደች። |
8. | ራሔልም። ብርቱ ትግልን ከእኅቴ ጋር ታገልሁ፥ አሸነፍሁም አለች፤ ስሙንም ንፍታሌም ብላ ጠራችው። |
9. | ልያም መውለድን እንዳቆመች ባየች ጊዜ ባሪያዋን ዘለፋን ወሰደች፥ ሚስት ትሆነውም ዘንድ ለያዕቆብ ሰጠችው። |
10. | የልያ ባሪያ ዘለፋም ወንድ ልጅን ለያዕቆብ ወለደች። |
11. | ልያም። ጉድ አለች፤ ስሙንም ጋድ ብላ ጠራችው። |
12. | የልያ ባሪያ ዘለፋም ዳግመኛ ለያዕቆብ ወንድ ልጅን ወለደች። |
13. | ልያም። ደስታ ሆነልኝ፤ ሴቶች ያመሰግኑኛልና አለች፤ ስሙንም አሴር ብላ ጠራችው። |
14. | ሮቤል ስንዴ በሚታጨድበት ወራት ወጣ፥ በእርሻም እንኮይ አገኘ፥ ለእናቱ ለልያም አመጣላት። ራሔልም ልያን። የልጅሽን እንኮይ ስጪኝ አለቻት። |
15. | እርስዋም። ባሌን መውሰድሽ በውኑ ጥቂት ነገር ነውን? አሁን ደግሞ የልጄን እንኮይ ልትወስጂ ትፈልጊያለሽን? አለቻት። ራሔልም። እንኪያስ ስለ ልጅሽ እንኮይ በዚህች ሌሊት ከአንቺ ጋር ይተኛ አለች። |
16. | ያዕቆብም ሲመሽ ከዱር ገባ፥ ልያም ልትቀበለው ወጣች እንዲህም አለችው። ወደ እኔ ትገባለህ፤ በልጄ እንኮይ በእርግጥ ተከራይቼሃለሁና። በዚያችም ሌሊት ከእርስዋ ጋር ተኛ። |
17. | እግዚአብሔርም የልያን ጸሎት ሰማ፥ ፀነሰችም፥ አምስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች። |
18. | ልያም። ባሪያዬን ለባሌ ስለ ሰጠሁ እግዚአብሔር ዋጋዬን ሰጠኝ አለች፤ ስሙንም ይሳኮር ብላ ጠራችው። |
19. | ልያም ደግማ ፀነሰች፥ ስድስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች። |
20. | ልያም። እግዚአብሔር መልካም ስጦታን ሰጠኝ፤ እንግዲህስ ባሌ ከእኔ ጋር ይኖራል፥ ስድስት ልጆችን ወልጄለታለሁና አለች፤ ስሙንም ዛብሎን ብላ ጠራችው። |
21. | ከዚያም በኋላ ሴት ልጅን ወለደች፥ ስምዋንም ዲና አለቻት። |
22. | እግዚአብሔርም ራሔልን አሰበ፥ እግዚአብሔርም ተለመናት፥ ማኅፀንዋንም ከፈተላት፤ |
23. | ፀነሰችም፥ ወንድ ልጅንም ወለደችና። እግዚአብሔር ስድቤን አስወገደ አለች፤ |
24. | ስሙንም። እግዚአብሔር ሁለተኛ ወንድ ልጅን ይጨምርልኝ ስትል ዮሴፍ ብላ ጠራችው። |
25. | ራሔልም ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው። ወደ ስፍራዬ ወደ አገሬም እመለስ ዘንድ አሰናብተኝ። |
26. | ስለ እነርሱ የተገዛሁላቸውን ሚስቶቼንና ልጆቼን ስጠኝና ልሂድ፤ የተገዛሁልህን መገዛት ታውቃለህና። |
27. | ላባም። በዓይንህ ፊት ሞገስን የማገኝ ብሆንስ ከዚሁ ተቀመጥ፤ እግዚአብሔር በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ ተመልክቼአለሁና አለው። |
28. | ደመወዝህን ንገረኝ፥ እርሱንም እሰጥሃለሁ አለ። |
29. | እርሱም አለው። እንዴት እንዳገለገልሁህ፥ ከብትህንም እንዴት እንደ ጠበቅሁልህ አንተ ታውቃለህ። |
30. | ከእኔ መምጣት በፊት የነበረህ ጥቂት ነበርና፥ ዛሬም እጅግ በዛ፤ ወደ አንተ በመምጣቴም እግዚአብሔር ባረክህ፤ አሁንም እኔ ደግሞ ለቤቴ የምሠራው መቼ ነው? |
31. | እርሱም። የምሰጥህ ምንድር ነው? አለ። ያዕቆብም አለው። ምንም አትስጠኝ፤ ይህንም ነገር ብታደርግልኝ እንደ ገና በጎችህን አበላለሁ እጠብቃለሁም። |
32. | ዛሬ በመንጎችህ በኩል አልፋለሁ፥ በዚያም ከበጎችህ መካከል ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለበቱን ጥቁሩንም በግ ሁሉ፥ ከፍየሎቹም ነቍጣና ዝንጕርጕር ያለበቱን እለያለሁ፤ እነርሱም ደመወዜ ይሆናሉ። |
33. | ስለዚህም በፊትህ ያለውን ደመወዜን ለመመልከት በመጣህ ጊዜ ወደ ፊት ጻድቅነቴ ይመሰክርልኛል፤ ከፍየሎች ዝንጕርጕርና ነቍጣ የሌለበት ከበግ ጠቦቶችም ጥቁር ያልሆኑ ሁሉ፥ እርሱ በእኔ ዘንድ ቢገኝ እንደ ተሰረቀ ይቆጠርብኝ። |
34. | ላባም። እነሆ እንደ ቃልህ ይሁን አለ። |
35. | በዚያም ቀን ከተባቶቹ ፍየሎች ሽመልመሌ መሳይና ነቍጣ ያለባቸውን፥ ከእንስቶቹም ፍየሎች ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለባቸውን፥ ነጭ ያለበትን ማንኛውንም ሁሉ፥ ከበጎቹም መካከል ጥቁሩን በግ ሁሉ ለይቶ ለልጆቹ ሰጣቸው። |
36. | በእርሱና በያዕቆብ መካከልም የሦስት ቀን መንገድ ያህል አራቃቸው፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን በጎች ይጠብቅ ነበር። |
37. | ያዕቆብም ልብን ለውዝ ኤርሞን ከሚባሉ እንጨቶች እርጥብ በትርን ወስዶ በበትሮቹ ውስጥ ያለው ነጭ እንዲታይ ነጭ ሽመልመሌ አድርጎ ላጣቸው። |
38. | የላጣቸውንም በትሮች በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ በበጎቹ ፊት አኖራቸው፤ በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ ይጎመጁ ነበር። |
39. | በጎቹም በትሮቹን አይተው ከመጎምጀታቸው የተነሣ ፀነሱ፤ በጎቹም ሽመልመሌ መሳይና ዝንጕርጕር ነቍጣም ያለበቱን ወለዱ። |
40. | ያዕቆብም ጠቦቶቹን ለየ፥ ሽመልመሌ መሳይና ጥቁር ያለባቸውን በጎቹንም ሁሉ በላባ በጎች ፊት ለፊት አኖረ፤ መንጎቹንም ለብቻቸው አቆማቸው፥ ወደ ላባም በጎች አልጨመራቸውም። |
41. | እንዲህም ሆነ፤ የበረቱት በጎች በጎመጁ ጊዜ፥ በጎቹ በትሮቹን አይተው በበትሮቹ አምሳል ይፀንሱ ዘንድ ያዕቆብ በትሮቹን በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ ከበጎቹ ፊት አደረገ፤ |
42. | በደከሙ በጎችም ፊት በትሩን አያደርገውም ነበር፤ የደከሙትም ለላባ፥ የበረቱትም ለያዕቆብ ሆኑ። |
43. | ያ ሰውም እጅግ ባለ ጠጋ ሆነ፤ ብዙም ከብት ሴቶችም ወንዶችም ባሪያዎች ግመሎችም አህዮችም ሆኑለት። |
← Genesis (30/50) → |