| ← Genesis (25/50) → |
| 1. | አብርሃምም ደግሞ ስምዋ ኬጡራ የተባላች ሚስት አገባ። |
| 2. | እርስዋም ዘምራንን፥ ዮቅሳንን፥ ሜዳንን፥ ምድያምን፥ የስቦቅን፥ ስዌሕን ወለደችለት። |
| 3. | ዮቅሳንም ሳባንና ድዳንን ወለደ። የድዳንም ልጆች አሦርያውያን፥ ለጡሳውያን፥ ለኡማውያን ናቸው። |
| 4. | የምድያምም ልጆች ጌፌር፥ ዔፌር፥ ሄኖኅ፥ አቢዳዕ፥ ኤልዳዓ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው። |
| 5. | አብርሃምም የነበረውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጠው፤ |
| 6. | የአብርሃምም ለነበሩ ለቁባቶቹ ልጆች አብርሃም ስጦታን ሰጣቸው፤ እርሱም ገና በሕይወቱ ሳለ ከልጁ ከይስሐቅ ለይቶ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደ ምሥራቅ አገር ሰደዳቸው። |
| 7. | አብርሃምም የኖረበት የዕድሜው ዓመታት እነዚህ ናቸው፤ መቶ ሰባ አምስት ዓመት ኖረ። |
| 8. | አብርሃምም ነፍሱን ሰጠ፥ በመልካም ሽምግልናም ሞተ፤ ሸመገለም፥ ብዙ ዘመንም ጠገበ፤ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ። |
| 9. | ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤልም በመምሬ ፊት ለፊት ባለው በኬጢያዊ በሰዓር ልጅ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ ቀበሩት ። |
| 10. | አብርሃም ከኬጢ ልጆች የገዛው እርሻ ይህ ነው፤ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ። |
| 11. | አብርሃምም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን ባረከው፤ ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ በሚጠራው ምንጭ አጠገብ ኖረ። |
| 12. | የሣራ ባሪያ ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችው የአብርሃም ልጅ የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው፤ |
| 13. | የእስማኤልም የልጆቹ ስም በየስማቸውና በየትውልዳቸው እንዲህ ነው፤ የእስማኤል የበኵር ልጁ |
| 14. | ነባዮት፥ ቄዳር፥ ነብዳኤል፥ መብሳም፥ ማስማዕ፥ |
| 15. | ዱማ፥ ማሣ፥ ኩዳን፥ ቴማን፥ ኢጡር፥ ናፌስ፥ ቄድማ። |
| 16. | የእስማኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ስማቸውም በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው ይኸው ነው፤ በየወገናቸውም አሥራ ሁለት አለቆች ናቸው። |
| 17. | እስማኤልም የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው፤ ነፍሱን ሰጠ ሞተም፤ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ። |
| 18. | መኖሪያቸውም ከኤውላጥ አንሥቶ በግብፅ ፊት ለፊት እስከምትገኝ እስከ ሱር ድረስ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ ላይ ነበረ፤ እንዲህም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ተቀመጠ። |
| 19. | የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድም ይህ ነው፤ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ |
| 20. | ይስሐቅም አርባ ዓመት ሲሆነው ርብቃን አገባ፤ እርስዋም በሁለት ወንዞች መካከል ያለ የሶርያዊው የባቱኤል ልጅና የሶርያዊው የላባ እኅት ናት። |
| 21. | ይስሐቅም ስለሚስቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ መካን ነበረችና፤ እግዚአብሔርም ተለመነው፥ ርብቃም ሚስቱ ፀነሰች። |
| 22. | ልጆችም በሆድዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርስዋም። እንዲህ ከሆነ ይህ ለእኔ ምኔ ነው? አለች። ከእግዚአብሔርም ትጠይቅ ዘንድ ሄደች። |
| 23. | እግዚአብሔርም አላት። ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው፥ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል። |
| 24. | ትወልድ ዘንድ ዘመንዋ በተፈጸመ ጊዜም፥ እነሆ፥ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ። |
| 25. | በፊትም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንተናውም ጠጕር ለብሶ ነበር፤ ስሙም ዔሳው ተባለ። |
| 26. | ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፥ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስሙም ያዕቆብ ተባለ። እርስዋ ልጆችን በወለደቻቸው ጊዜ ይስሐቅ ስድሳ ዓመት ሆኖት ነበር። |
| 27. | ብላቴኖቹም አደጉ፤ ዔሳውም አደን የሚያውቅ የበረሃ ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በድንኳንም ይቀመጥ ነበር። |
| 28. | ይስሐቅም ዔሳውን ይወድ ነበር፥ ካደነው ይበላ ነበርና፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበረች። |
| 29. | ያዕቆብም ወጥ ሠራ፤ ዔሳውም ደክሞ ከበረሃ ገባ፤ |
| 30. | ዔሳውም ያዕቆብን። ከዚህ ከቀዩ ወጥ አብላኝ፥ እኔ እጅግ ደክሜአለሁና አለው፤ ስለዚህ ስሙ ኤዶም ተባለ። |
| 31. | ያዕቆብም። በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ አለው። |
| 32. | ዔሳውም። እነሆ፥ እኔ ልሞት ነኝ፤ ይህች ብኵርና ለምኔ ናት? አለ ። |
| 33. | ያዕቆብም። እስኪ በመጀመሪያ ማልልኝ አለው። ማለለትም፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠ። |
| 34. | ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ በላ፥ ጠጣ፥ ተነሥቶም ሄደ፤ እንዲሁም ዔሳው ብኵርናውን አቃለላት። |
| ← Genesis (25/50) → |