| ← Genesis (24/50) → |
| 1. | አብርሃምም ሸመገለ በዘመኑም አረጀ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሥራው ሁሉ ባረከው። |
| 2. | አብርሃምም ሎሌውን የቤቱን ሽማግሌ የከብቱን ሁሉ አዛዥ አለው። |
| 3. | እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ እኔም አብሬ ከምኖራቸው ከከነዓን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስት እንዳትወስድለት በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ |
| 4. | ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ተወላጆቼ ትሄዳለህ፥ ለልጄ ለይስሐቅም ሚስትን ትወስድለታለህ። |
| 5. | ሎሌውም። ሴቲቱ ምናልባት ወደዚህ አገር ከእኔ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደ ሆነ ልጅህን ወደ ወጣህበት አገር ልመልሰውን? አለው። |
| 6. | አብርሃምም አለው። ልጄን ወደዚያ እንዳትመልስ ተጠንቀቅ፤ |
| 7. | ከአባቴ ቤት ከተወለድሁባት ምድርም ያወጣኝ። ይህችንም ምድር እሰጥሃለሁ ብሎ የነገረኝና የማለልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ መልአኩን በፊትህ ይሰድዳል፥ ከዚያም ለልጄ ሚስትን ትወስዳለህ። |
| 8. | ሴቲቱም ከአንተ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደ ሆነ ከዚህ ካቀረብሁህ መሐላ ንጹሕ ነህ፤ ልጄን ግን ወደዚያ አትመልሰው። |
| 9. | ሎሌውም ከጌታው ከአብርሃም ጭን በታች እጁን አደረገ ስለዚሁም ነገር ማለለት። |
| 10. | ሎሌውም ከጌታው ግመሎች መካከል አሥር ግመሎችን ወስዶ፥ ከጌታውም ዕቃ መልካም መልካሙን ይዞ ተነሣ፤ ተነሥቶም ወደ መስጼጦምያ ወደ ናኮር ከተማ ሄደ። |
| 11. | ሲመሽም ሴቶች ውኃ ሊቀዱ በሚወጡበት ጊዜ ከከተማይቱ ውጪ በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ግመሎቹን አስበረከከ። |
| 12. | እንዲህም አለ። የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፥ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። |
| 13. | እነሆ፥ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ፥ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃውን ሊቀዱ ይመጣሉ፤ |
| 14. | ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት እርስዋም። አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ፥ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ። |
| 15. | ይህን መናገሩንም ሳይፈጽም እነሆ፥ ሚልካ የወለደችው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በጫንቃዋ ተሸክማ ወጣች፤ ሚልካም የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ናት። |
| 16. | ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች፤ ወደ ምንጭም ወረደች እንስራዋንም ሞላች፥ ተመልሳም ወጣች። |
| 17. | ሎሌውም ሊገናኛት ሮጠና። ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት። |
| 18. | እርስዋም። ጌታዬ ሆይ፥ ጠጣ አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን በእጅዋ አውርዳ አጠጣችው። |
| 19. | እርሱንም ካጠጣች በኋላ። ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ አለች። |
| 20. | ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው፥ ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጕድጓዱ ሮጠች፥ ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች። |
| 21. | ሰውዮውም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር፤ እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅም ዝም አለ። |
| 22. | ግመሎቹም ከጠጡ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ሰውዮው ግማሽ ሰቅል የሚመዘን የወርቅ ቀለበት፥ ለእጆችዋም አሥር ሰቅል የሚመዘን ጥንድ የወርቅ አምባር አወጣ፤ |
| 23. | እንዲህም አላት። አንቺ የማን ልጅ ነሽ? እስኪ ንገሪኝ፤ በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኛልን? |
| 24. | አለችውም። እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችው የባቱኤል ልጅ ነኝ። |
| 25. | በእኛ ዘንድ ገለባና ገፈራ የሚበቃ ያህል አለ፥ ለማደሪያም ደግሞ ስፍራ አለን። |
| 26. | ሰውዮውም አጎነበሰ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገደ ። |
| 27. | እንዲህም አለ። ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እኔ በመንገድ ሳለሁ እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ። |
| 28. | ብላቴናይቱም ሮጠች፥ ለእናትዋም ቤት ይህን ነገር ሁሉ ተናገረች። |
| 29. | ለርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ ላባም ወደ ውጪ ወደ ውኃው ምንጭ ወደ ሰውዮው ሮጠ። |
| 30. | ቀለበቱንና አምባሮቹን በእኅቱ እጅ ባየ ጊዜ፥ የእኅቱን የርብቃንም ነገር። ያ ሰው እንዲህ አለኝ ያለችውን በሰማ ጊዜ፥ እርሱ ወደዚያ ሰው መጣ፤ እነሆም፥ በውኃው ምንጭ አጠገብ ከግመሎቹ ዘንድ ቆሞ ነበር። |
| 31. | እርሱም አለው። አንተ የእግዚአብሔር ቡሩክ፥ ግባ፤ ስለምን አንተ በውጪ ቆመሃል? እኔም ቤቱን ለግመሎችህም ስፍራ አዘጋጅቼአለሁ። |
| 32. | ሰውዮውም ወደ ቤት ገባ፥ ግመሎቹንም አራገፈ፤ ገለባና ገፈራም ለግመሎቹ አቀረበ፤ እግሩን ይታጠብ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ላሉት ሰዎች እግር ውኃ አቀረበ። |
| 33. | መብልንም በፊቱ አቀረበለት፤ እርሱ ግን። ነገሬን እስክናገር ድረስ አልበላም አለ። እርሱም። ተናገር አለው። |
| 34. | እርሱም አለ። እኔ የአብርሃም ሎሌ ነኝ። |
| 35. | እግዚአብሔርም ጌታዬን እጅግ ባረከው፥ አገነነውም፤ በጎችንና ላሞችን፥ ብርንም፥ ወርቅንም፥ ወንዶች ባሪያዎችንና ሴቶች ባሪያዎችን፥ ግመሎችንም አህዮችንም ሰጠው። |
| 36. | ሣራም የጌታዬ ሚስት በእርጅናው ለጌታዬ ወንድ ልጅን ወለደች፤ የነበረውንም ሁሉ ሰጠው። |
| 37. | ጌታዬም እንዲህ ሲል አማለኝ። እኔ ካለሁበት አገር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስትን አትውሰድ |
| 38. | ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት ወደ ወገኔም ሂድ፥ ለልጄም ሚስትን ውሰድለት። |
| 39. | ጌታዬንም። ሴቲቱ ምናልባት ባትከተለኝሳ? አልሁት። |
| 40. | እርሱም አለኝ። አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁለት እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፥ መንገድህንም ያቀናል። ለልጄም ከወገኖቼ ከአባቴም ቤት ሚስትን ትወስዳለህ፤ |
| 41. | የዚያን ጊዜ ከመሐላዬ ንጹሕ ነህ፤ ወደ ዘመዶቼ ሄደህ እነርሱ ባይሰጡህ ካማልሁህ መሐላ ንጹሕ ትሆናለህ። |
| 42. | ዛሬም ወደ ውኃው ምንጭ መጣሁ፥ እንዲህም አልሁ። የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የምሄድበትን መንገዴን ብታቀናልኝ፤ |
| 43. | እነሆ፥ እኔ በውኃው ምንጭ ላይ ቆሜአለሁ፤ ውኃ ልትቀዳ ለምትመጣውም ቆንጆ። ጥቂት ውኃ ከእንስራሽ አጠጪኝ ስላት፥ |
| 44. | እርስዋም። አንተ ጠጣ፥ ደግሞም ለግመሎችህ እቀዳለሁ የምትለኝ፥ እግዚአብሔር ለጌታዬ ልጅ ያዘጋጃት ሴት እርስዋ ትሁን። |
| 45. | እኔም የልቤን መናገር ገና ሳልፈጽም፥ እነሆ፥ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ወጣች፥ ወደ ምንጭም ወርዳ ውኃ ቀዳች፤ እኔም። እስኪ አጠጪኝ አልኋት። |
| 46. | ፈጥናም እንስራዋን ከጫንቃዋ አወረደችና። አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህንም ደግሞ አጠጣለሁ አለች፤ እኔም ጠጣሁ፥ ግመሎቼንም ደግሞ አጠጣች። |
| 47. | እኔም። አንቺ የማን ልጅ ነሽ? ብዬ ጠየቅኋት። እርስዋም። ሚልካ ለናኮር የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ አለች፤ ቀለበትም አደረግሁላት፥ ለእጆችዋም አምባሮች አደረግሁላት። |
| 48. | በግምባሬም አጎነበስሁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገድሁ፤ የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። |
| 49. | አሁንም ቸርነትና እውነት ለጌታዬ ትሠሩ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ ይህም ባይሆን ንገሩኝ፥ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እል ዘንድ። |
| 50. | ላባና ባቱኤልም መለሱ እንዲህም አሉ። ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶአል ክፉም በጎም ልንመልስልህ አንችልም። |
| 51. | ርብቃ እንኋት በፊትህ ናት፤ ይዘሃት ሂድ፥ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህም ልጅ ሚስት ትሁን። |
| 52. | የአብርሃምም ሎሌ ነገራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ምድር ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ። |
| 53. | ሎሌውም የብርና የወርቅ ጌጥ ልብስም አወጣ፥ ለርብቃም ሰጣት፤ የከበረ ስጦታንም ለወንድምዋና ለእናትዋ አቀረበ። |
| 54. | እርሱም ከእርሱም ጋር ያሉት በሉ ጠጡም፥ ከዚያም አደሩ፤ ማልደውም ተነሡና። ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው ። |
| 55. | ወንድምዋና እናትዋም። ብላቴናይቱ አንድ አሥር ቀን ያህል እንኳ ከእኛ ዘንድ ትቀመጥ፤ ከዚያም በኋላ ትሄዳለች አሉ። |
| 56. | እርሱም። እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው። |
| 57. | እነርሱም። ብላቴናይቱን እንጥራና ከአፍዋ እንጠይቅ አሉ። |
| 58. | ርብቃንም ጠርተው። ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን? አሉአት። እርስዋም። እሄዳለሁ አለች። |
| 59. | እኅታቸውንም ርብቃን ሞግዚትዋንም የአብርሃምን ሎሌና ሰዎቹንም አሰናበቱአቸው። |
| 60. | ርብቃንም መረቁአትና። አንቺ እኅታችን፥ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ አሉአት። |
| 61. | ርብቃም ተነሣች ደንገጥሮችዋም፥ በግመሎችም ላይ ተቀምጠው ያንን ሰው ተከተሉት፤ ሎሌውም ርብቃን ተቀብሎ ሄደ። |
| 62. | ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ በሚሉአት ምንጭ መንገድ መጣ፤ በአዜብ ምድር ተቀምጦ ነበርና። |
| 63. | ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር፤ ዓይኖቹንም አቀና፥ እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ። |
| 64. | ርብቃም ዓይኖችዋን አቀናች፥ ይስሐቅንም አየች፥ ከግመልም ወረደች። |
| 65. | ሎሌውንም። ሊገናኘን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማን ነው? አለችው። ሎሌውም። እርሱ ጌታዬ ነው አላት፤ እርስዋም መሸፈኛ ወስዳ ተከናነበች። |
| 66. | ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። |
| 67. | ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት፥ ርብቃንም ወሰዳት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወደዳትም፤ ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና። a |
| ← Genesis (24/50) → |