| ← Genesis (21/50) → |
| 1. | እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ሣራን አሰበ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ለሣራ አደረገላት። |
| 2. | ሣራም ፀነሰች፥ እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት። |
| 3. | አብርሃምም የተወለደለትን ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው። |
| 4. | አብርሃምም ልጁን ይስሐቅን እግዚአብሔር እንዳዘዘው በስምንተኛ ቀን ገረዘው። |
| 5. | አብርሃምም ልጁ ይስሐቅ በተወለደለት ጊዜ የመቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ። |
| 6. | ሣራም። እግዚአብሔር ሳቅ አድርጎልኛል፤ ይህንንም የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል አለች። |
| 7. | ደግሞም። ሣራ ልጆችን እንድታጠባ ለአብርሃም ማን በነገረው? በእርጅናው ልጅን ወልጄለታለሁና አለች። |
| 8. | ሕፃኑም አደገ፥ ጡትንም ከመጥባት ተቋረጠ፤ አብርሃምም ይስሐቅን ጡት ባስጣለበት ቀን ትልቅ ግብዣን አደረገ። |
| 9. | ሣራም ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን ልጅ ሲስቅ አየችው። |
| 10. | አብርሃምንም። ይህችን ባሪያ ከነልጅዋ አሳድድ፤ የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስምና አለችው። |
| 11. | ይህም ነገር በአብርሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነበት። |
| 12. | እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። ስለ ባሪያህና ስለ ብላቴናው አትዘን፤ ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ፤ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና። |
| 13. | የባሪያይቱን ልጅ ደግሞ ሕዝብ አደርገዋለሁ፥ ዘርህ ነውና። |
| 14. | አብርሃምም ማልዶ ተነሣ፥ እንጀራንም ወሰደ፥ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትከሻዋ አሸከማት፥ ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት፤ እርስዋም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቅበዘበዘች። |
| 15. | ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፤ ብላቴናውንም ከአንድ ቍጥቋጦ በታች ጣለችው፤ |
| 16. | እርስዋም ሄደች። ብላቴናው ሲሞት አልየው ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች፥ ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች። |
| 17. | እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት። አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። |
| 18. | ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው፤ ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና። |
| 19. | እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት፥ የውኃ ጕድጓድንም አየች፤ ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች፥ ብላቴናውንም አጠጣች። |
| 20. | እግዚአብሔርም ከብላቴናው ጋር ነበረ፤ አደገም፥ በምድረ በዳም ተቀመጠ፥ ቀስተኛም ሆነ። |
| 21. | በፋራን ምድረ በዳም ተቀመጠ፤ እናቱም ከምድረ ግብፅ ሚስት ወሰደችለት። |
| 22. | በዚያም ዘመን አቢሜሌክ ከሙሽራው ወዳጅ ከአኮዘትና ከሠራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋር አብርሃምን አለው። በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ |
| 23. | አሁንም በእኔም በልጄም በልጅ ልጄም ክፉ እንዳታደርግብኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ፤ ነገር ግን ለአንተ ቸርነትን እንዳደረግሁ አንተም ለእኔ ለተቀመጥህባትም ምድር ቸርነትን ታደርጋለህ። |
| 24. | አብርሃምም። እኔ እምላለሁ አለ። |
| 25. | አቢሜሌክንም ባሪያዎቹ በነጠቁት በውኃ ጕድጓድ ምክንያት አብርሃም ወቀሰው። |
| 26. | አቢሜሌክም አለ። ይህን ነገር ያደረገውን አላወቅሁም፤ አንተም ደግሞ ምንም አልነገርኸኝም፥ እኔም ከዛሬ በቀር አልሰማሁም። |
| 27. | አብርሃምም በጎችንና ላሞችን አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን አደረጉ። |
| 28. | አብርሃምም ሰባት ቄቦች በጎችን ለብቻቸው አቆመ። |
| 29. | አቢሜሌክም አብርሃምን። ለብቻቸው ያቆምሃቸው እነዚህ ሰባት ቄቦች በጎች ምንድር ናቸው? አለው። |
| 30. | እርሱም። እኔ ይህችን የውኃ ጕድጓድ እንደቆፈርሁ ምስክር ይሆንልኝ ዘንድ እነዚህን ሰባት ቄቦች በጎች ከእጄ ትወስዳለህ አለው። |
| 31. | ስለዚህ የዚያን ስፍራ ስም ቤርሳቤህ ብሎ ጠራው፤ ከዚያ ሁለቱ ተማምለዋልና። |
| 32. | በቤርሳቤህም ቃል ኪዳንን አደረጉ። አቢሜሌክና የሙሽራው ወዳጅ አኮዘት የሠራዊቱ አለቃ ፊኮልም ተነሥተው ወደ ፍልስጥኤም ምድር ተመለሱ። |
| 33. | አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍን ተከለ፤ በዚያም የዘላለሙን አምላክ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ። |
| 34. | አብርሃምም በፍልስጥኤም ምድር ብዙ ቀን እንግዳ ሆኖ ተቀመጠ። |
| ← Genesis (21/50) → |