Genesis (20/50)  

1. አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ አዜብ ምድር ሄደ፥ በቃዴስና በሱር መካከልም ተቀመጠ፤ በጌራራም በእንግድነት ተቀመጠ።
2. አብርሃምም ሚስቱን ሣራን። እኅቴ ናት አለ፤ የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክም ላከና ሣራን ወሰዳት።
3. እግዚአብሔርም ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጣ፥ እንዲህም አለው። እነሆ፥ አንተ ስለ ወሰድሃት ሴት ምውት ነህ፤ እርስዋ ባለ ባል ናትና።
4. አቢሜሌክ ግን አልቀረባትም ነበር፤ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ ጻድቁን ሕዝብ ደግሞ ታጠፋለህን?
5. እኅቴ ናት ያለኝ እርሱ አይደለምን? እርስዋም ደግሞ ራስዋ። ወንድሜ ነው አለች፤ በልቤ ቅንነትና በእጄ ንጹሕነት ይህንን አደረግሁ።
6. እግዚአብሔርም በሕልም አለው። ይህን በልብህ ቅንነት እንዳደረግህ እኔ አወቅሁ፥ እኔም ደግሞ በፊቴ ኃጢአትን እንዳትሠራ ከለከልሁህ፤ ስለዚህም ትነካት ዘንድ አልተውሁም።
7. አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ፤ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንድትሞት ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንዲሞት በእርግጥ እወቅ።
8. አቢሜሌክም በነገታው ማለደ፥ ባሪያዎቹንም ሁሉ ጠራ፥ ይህንንም ነገር ሁሉ በጆሮአቸው ተናገረ፤ ሰዎቹም እጅግ ፈሩ።
9. አቢሜሌክም አብርሃምን ጠርቶ አለው። ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ምንስ ክፉ ሠራሁብህ? በእኔና በመንግሥቴ ላይ ትልቅ ኃጢአት አውርደሃልና፤ የማይገባ ሥራ በእኔ ሠራህብኝ።
10. አቢሜሌክም አብርሃምን አለው። ይህን ማድረግህ ምን አይተህ ነው?
11. አብርሃምም አለ። በዚህ ስፍራ እግዚአብሔርን መፍራት በእውነት እንደሌለ፥ ለሚስቴም ሲሉ እንደሚገድሉኝ ስላሰብሁ ነው።
12. እርስዋም ደግሞ በእውነት እኅቴ ናት፤ የእናቴ ልጅ አይደለችም እንጂ የአባቴ ልጅ ናት፤ ለእኔም ሚስት ሆነች።
13. እግዚአብሔርም ከአባቴ ቤት ባወጣኝ ጊዜ አልኋት። በገባንበት አገር ሁሉ ለእኔ የምታደርጊው ወሮታ ይህ ነው። ወንድሜ ነው ብለሽ ስለ እኔ ተናገሪ።
14. አቢሜሌክም በጎችንና ላሞችን ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችን አመጣ፥ ለአብርሃምም ሰጠው፥ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት።
15. አቢሜሌክም። እነሆ፥ ምድሬ በፊትህ ናት፤ በወደድኸው ተቀመጥ አለ።
16. ሣራንም አላት። እነሆ፥ ለወንድምሽ ሺህ ሚዛን ብር ሰጠሁት፤ ያም እነሆ ከአንቺ ጋር ባሉት ሁሉ ፊት የዓይኖች መሸፈኛ ይሁንሽ፤ ጽድቅሽ ለሰዎች ሁሉ ተገልጦአልና።
17. አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አቢሜሌክን ሚስቱንም ባሪያዎቹንም ፈወሳቸው፥ እነርሱም ወለዱ፤
18. እግዚአብሔር በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት በአቢሜሌክ ቤት ማኅፀኖችን ሁሉ በፍጹም ዘግቶ ነበርና። a

  Genesis (20/50)