← Genesis (18/50) → |
1. | በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት። |
2. | ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥ እንዲህም አለ። |
3. | አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፤ |
4. | ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፤ |
5. | ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፤ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና። እነርሱም። እንዳልህ አድርግ አሉት። |
6. | አብርሃምም ወደ ድንኳን ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባና። ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፥ ለውሺውም፥ እንጎቻም አድርጊ አላት። |
7. | አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሮጠ፥ እጅግ የሰባም ታናሽ ጥጃ ያዘና ለብላቴናው ሰጠው፥ ያዘጋጅም ዘንድ ተቻኰለ። |
8. | እርጎና ወተትም ያዘጋጀውንም ጥጃ አመጣ፥ በፊታቸውም አቀረበው፤ እርሱም ከዛፉ በታች በፊታቸው ቆሞ ነበር፥ እነርሱም በሉ። |
9. | እነርሱም። ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? አሉት። እርሱም። በድንኳኑ ውስጥ ናት አላቸው። |
10. | እርሱም። የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች። |
11. | አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፤ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። |
12. | ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች። ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል። |
13. | እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? |
14. | በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታገኛለች። |
15. | ሣራም ስለ ፈራች። አልሳቅሁም ስትል ካደች። እርሱም። አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ አላት። |
16. | ሰዎቹም ከዚያ ተነሥተው ወደ ሰዶም አቀኑ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ሄደ። |
17. | እግዚአብሔርም አለ። እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን? |
18. | አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናልና፥ የምድር አሕዛብም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉና። |
19. | ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንዲያዝዝ አውቃለሁና፤ ይህም እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ የተናገረውን ነገር ሁሉ ያመጣ ዘንድ ነው። |
20. | እግዚአብሔርም አለ። የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና፥ |
21. | እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ ወርጄ አያለሁ፤ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ። |
22. | ሰዎቹም ከዚያ ፊታቸውን አቀኑ፥ ወደ ሰዶምም ሄዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት ገና ቆሞ ነበር። |
23. | አብርሃምም ቀረበ አለም። በውኑ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ታጠፋለህን? |
24. | አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱንስ በእርስዋ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን? |
25. | ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፥ ጻድቁም እንደ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን? |
26. | እግዚአብሔርም። በሰዶም በከተማይቱ ውስጥ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ስፍራውን ሁሉ ስለ እነርሱ እምራለሁ አለ። |
27. | አብርሃምም መለሰ አለም። እኔ አፈርና አመድ ስሆን ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ እነሆ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፤ |
28. | ከአምሳው ጻድቃን አምስት ቢጐድሉ ከተማይቱን ሁሉ በአምስቱ ምክንያት ታጠፋለህን? ከዚያ አርባ አምስት ባገኝ አላጠፋትም አለ። |
29. | ደግሞም ተናገረው፥ እንዲህም አለ። ምናልባት ከዚያ አርባ ቢገኙሳ? እርሱም። ለአርባው ስል አላደርገውም አለ። |
30. | እርሱም። ጌታዬ አይቆጣ እኔም እናገራለሁ ምናልባት ከዚያ ሠላሳ ቢገኙሳ? አለ። እርሱም ከዚያ ሰላሳ ባገኝ አላጠፋም አለ። |
31. | ደግሞም። እነሆ፥ ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፤ ምናልባት ከዚያ ሀያ ቢገኙሳ? አለ። እርሱም። ከዚያ ሀያ ቢገኙ ስለ ሀያው አላደርገውም አለ። |
32. | እርሱም። እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ብናገር ጌታዬ አይቆጣ፤ ምናልባት ከዚያ አሥር ቢገኙሳ? አለ። እርሱም። ስለ አሥሩ አላጠፋትም አለ። |
33. | እግዚአብሔርም ከአብርሃም ጋር ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ስፍራው ተመለሰ። a |
← Genesis (18/50) → |