| ← Genesis (17/50) → |
| 1. | አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና። እኔ ኤልሻዳይ ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን፤ |
| 2. | ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ አለው። |
| 3. | አብራምም በግምባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው። እነሆ፥ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው፤ |
| 4. | ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። |
| 5. | ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራ፥ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። |
| 6. | እጅግም አበዛሃለሁ፥ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። |
| 7. | ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘላለም ኪዳን አቆማለሁ፥ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ። |
| 8. | በእንግድነት የምትኖርባትን ምድር፥ የከነዓን ምድር ሁሉ፥ ለዘላለም ግዛት ይሆንህ ዘንድ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ አምላክም እሆናቸዋለሁ። |
| 9. | እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፥ አንተ ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው። |
| 10. | በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔ ይህ ነው፤ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። |
| 11. | የቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። |
| 12. | የስምንት ቀን ልጅ ይገረዝ፤ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያይደለ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ፥ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገረዝ። |
| 13. | በቤትህ የተወለደ በብርህም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ። ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘላለም ቃል ኪዳን ይሆናል። |
| 14. | የቍልፈቱን ሥጋ ያልተገረዘ ቈላፍ ሰው ሁሉ፥ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ፤ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና። |
| 15. | እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። የሚስትህን የሦራን ስም ሦራ ብለህ አትጥራ፥ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ። |
| 16. | እባርካታለሁ፥ ደግሞም ከእርስዋ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ እባርካትማለሁ፥ የአሕዛብም እናት ትሆናለች፤ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርስዋ ይወጣሉ። |
| 17. | አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ በልቡም አለ። የመቶ ዓመት ሰው በውኑ ልጅ ይወልዳልን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን? |
| 18. | አብርሃምም እግዚአብሔርን። እስማኤል በፊትህ ቢኖር በወደድሁ ነበር አለው። |
| 19. | እግዚአብሔርም አለ። በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘላለም ቃል ኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ። |
| 20. | ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፤ እነሆ ባርኬዋለሁ፥ ፍሬያምም አደርገዋለሁ፥ እጅግም አበዛዋለሁ፤ አሥራ ሁለት አለቆችንም ይወልዳል፥ ታላቅ ሕዝብም እንዲሆን አደርገዋለሁ። |
| 21. | ቃል ኪዳኔን ግን በሚመጣው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ። |
| 22. | ንግግሩንም ከእርሱ ጋር በፈጸመ ጊዜ እግዚአብሔር ከአብርሃም ተለይቶ ወጣ። |
| 23. | አብርሃምም ልጁን እስማኤልን፥ በቤቱም የተወለዱትን ሁሉ፥ በብሩም የገዛቸውን ሁሉ፥ ከአብርሃም ቤተ ሰብ ወንዶቹን ሁሉ ወሰደ፥ የቍልፈታቸውንም ሥጋ እግዚአብሔር እንዳለው በዚያው ቀን ገረዘ። |
| 24. | አብርሃምም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው ነበረ፤ |
| 25. | ልጁ እስማኤልም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የአሥራ ሦስት ዓመት ልጅ ነበረ። |
| 26. | በዚያው ቀን አብርሃም ተገረዘ፥ ልጁ እስማኤልም። |
| 27. | በቤት የተወለዱትና በብር ከእንግዶች የተገዙት የቤቱ ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ተገረዙ። |
| ← Genesis (17/50) → |