| ← Genesis (15/50) → |
| 1. | ከዚህ ነገር በኋላም የእግዚአብሔር ቃል በራእይ ወደ አብራም መጣ፥ እንዲህ ሲል። አብራም ሆይ፥ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው። |
| 2. | አብራምም። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ ምንን ትሰጠኛለህ? እኔም ያለ ልጅ እሄዳለሁ፤ የቤቴም መጋቢ የደማስቆ ሰው ይህ ኤሊዔዘር ነው አለ። |
| 3. | አብራምም። ለእኔ ዘር አልሰጠኸኝም፤ እነሆም፥ በቤቴ የተወለደ ሰው ይወርሰኛል አለ። |
| 4. | እነሆም፥ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት። ይህ አይወርስህም፤ ነገር ግን ከጉልበትህ የሚወጣው ይወርስሃል። |
| 5. | ወደ ሜዳም አወጣውና። ወደ ሰማይ ተመልከት፥ ከዋክብትንም ልትቈጥራቸው ትችል እንደ ሆነ ቍጠር አለው። ዘርህም እንደዚሁ ይሆናል አለው። |
| 6. | አብራምም በእግዚአብሔር አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት። |
| 7. | ይህችን ምድር ትወርሳት ዘንድ እንድሰጥህ ከከለዳውያን ዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ አለው። |
| 8. | አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድወርሳት በምን አውቃለሁ? አለ። |
| 9. | እርሱም። የሦስት ዓመት ጊደር፥ የሦስት ዓመት ፍየልም፥ የሦስት ዓመት በግም፥ ዋኖስም፥ ርግብም ያዝልኝ አለው። |
| 10. | እነዚህንም ሁሉ ወሰደለት፥ በየሁለትም ከፈላቸው፥ የተከፈሉትንም በየወገኑ ትይዩ አደረጋቸው፤ ወፎችን ግን አልከፈለም። |
| 11. | አሞራዎችም በሥጋው ላይ ወረዱ፥ አብራምም አበረራቸው። |
| 12. | ፀሐይም በገባች ጊዜ በአብራም ከባድ እንቅልፍ መጣበት፤ እነሆም፥ ድንጋጤና ታላቅ ጨለማ ወደቀበት፤ |
| 13. | አብራምንም አለው። ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ እወቅ፤ ባሪያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል። |
| 14. | ደግሞም በባርነት በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርዳለሁ፤ ከዚያም በኋላ በብዙ ከብት ይወጣሉ። q2 ኤሊዔዘር የተባለውን የግዕዙን መጽሐፍ ኢያውብር ይለዋል። |
| 15. | አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ። |
| 16. | በአራተኛው ትውልድ ግን ወደዚህ ይመለሳሉ፤ የአሞራውያን ኃጢአት ገና አልተፈጸመምና። |
| 17. | ፀሐይም በገባች ጊዜ ታላቅ ጨለማ ሆነ፤ የምድጃ ጢስና የእሳት ነበልባል በዚያ በተከፈለው መካከል አለፈ። |
| 18. | በዚያ ቀን እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን አደረገ። ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ትልቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ይህችን ምድር ለዘርህ ሰጥቼአለሁ፤ |
| 19. | ቄናውያንን ቄኔዛውያንንም |
| 20. | ቀድሞናውያንንም ኬጢያውያንንም |
| 21. | ፌርዛውያንንም ራፋይምንም አሞራውያንንም ከነዓናውያንንም ጌርጌሳውያንንም ኢያቡሳውያንንም። |
| ← Genesis (15/50) → |