| ← Genesis (13/50) → |
| 1. | አብራምም ከግብፅ ወጣ፤ እርሱና ሚስቱ ለእርሱ የነበረውም ሁሉ ሎጥም ከእርሱ ጋር ወደ አዜብ ወጡ። |
| 2. | አብራምም በከብት በብርና በወርቅ እጅግ በለጠገ። |
| 3. | ከአዜብ ባደረገው በጕዞውም ወደ ቤቴል በኩል ሄደ፤ ያም ስፍራ አስቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳን ተክሎበት የነበረው ነው፤ |
| 4. | ያም ስፍራ አስቀድሞ መሠውያ የሠራበት ነው፤ በዚያም አብራም የእግዚአብሔርን ስም ጠራ። |
| 5. | ከአብራም ጋር የሄደው ሎጥ ደግሞ የላምና የበግ መንጋ ድንኳንም ነበረው። |
| 6. | በአንድነትም ይቀመጡ ዘንድ ምድር አልበቃቸውም የነበራቸው እጅግ ነበረና በአንድነት ሊቀመጡ አልቻሉም። |
| 7. | የአብራምንና የሎጥን መንጎች በሚጠብቁት መካከልም ጠብ ሆነ በዚያም ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያች ምድር ተቀምጠው ነበር። |
| 8. | አብራምም ሎጥን አለው። እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ። |
| 9. | ምድር ሁሉ በፊትህ አይደለችምን? ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ። |
| 10. | ሎጥም ዓይኑን አነሣ፥ በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውንም አገር ሁሉ ውኃ የሞላበት መሆኑን አየ፤ እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ አስቀድሞ እስከ ዞዓር ድረስ እንደ እግዚአብሔር ገነት በግብፅ ምድር አምሳል ነበረ። |
| 11. | ሎጥም በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውን አገር ሁሉ መረጠ፤ ሎጥም ወደ ምሥራቅ ተጓዘ፤ አንዱም ከሌላው እርስ በርሳቸው ተለያዩ። |
| 12. | አብራም በከነዓን ምድር ተቀመጠ ሎጥም በአገሩ ሜዳ ባሉት ከተሞች ተቀመጠ፥ እስከ ሰዶምም ድረስ ድንኳኑን አዘዋወረ። |
| 13. | የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ። |
| 14. | ሎጥ ከተለየው በኋላም እግዚአብሔር አብራምን አለው። ዓይንህን አንሣና አንተ ካለህበት ስፍራ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ እይ፤ |
| 15. | የምታያትን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁና። |
| 16. | ዘርህንም እንደ ምድር አሸዋ አደርጋለሁ፤ የምድርን አሸዋን ይቈጥር ዘንድ የሚችል ሰው ቢኖር ዘርህ ደግሞ ይቈጠራል። |
| 17. | ተነሣ በምድር በርዝመትዋም በስፋትዋም ሂድ እርስዋን ለአንተ እሰጣለሁና። |
| 18. | አብራምም ድንኳኑን ነቀለ መጥቶም በኬብሮን ባለው በመምሬ የአድባር ዛፍ ተቀመጠ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ። |
| ← Genesis (13/50) → |