| ← Genesis (12/50) → |
| 1. | እግዚአብሔርም አብራምን አለው። ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። |
| 2. | ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤ |
| 3. | የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ። |
| 4. | አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ፤ ሎጥም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ አብራምም ከካራን በወጣ ጊዜ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ። |
| 5. | አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን፥ ያገኙትን ከብት ሁሉና በካራን ያገኙአቸውን ሰዎች ይዞ ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ወጣ፤ ወደ ከነዓንም ምድር ገቡ። |
| 6. | አብራምም እስከ ሴኬም ስፍራ እስከ ሞሬ የአድባር ዛፍ ድረስ በምድር አለፈ፤ የከነዓን ሰዎችም በዚያን ጊዜ በምድሩ ነበሩ። |
| 7. | እግዚአብሔርም ለአብራም ተገለጠለትና። ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ አለው። እርሱም ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ ስፍራ መሠውያን ሠራ። |
| 8. | ከዚያም በቤቴል ምሥራቅ ወዳለው ተራራ ወጣ፥ በዚያም ቤቴልን ወደ ምዕራብ ጋይን ወደ ምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ። |
| 9. | አብራምም ከዚያ ተነሣ፥ እየተጓዘም ወደ አዜብ ሄደ። |
| 10. | በምድርም ራብ ሆነ፤ አብራምም በዚያ በእንግድነት ይቀመጥ ዘንድ ወደ ግብፅ ወረደ፥ በምድር ራብ ጸንቶ ነበርና። |
| 11. | ወደ ግብፅም ለመግባት በቀረበ ጊዜ ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት። አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ እነሆ እኔ አውቃለሁ |
| 12. | የግብፅ ሰዎች ያዩሽ እንደ ሆነ። ሚስቱ ናት ይላሉ እኔንም ይገድሉኛል፥ አንቺንም በሕይወት ይተዉሻል። |
| 13. | እንግዲህ በአንቺ ምክንያት መልካም ይሆንልኝ ዘንድ፥ ስለ አንቺም ነፍሴ ትድን ዘንድ። እኅቱ ነኝ በዪ። |
| 14. | አብራምም ወደ ግብፅ በገባ ጊዜ የግብፅ ሰዎች ሴቲቱን እጅግ ውብ እንደ ሆነች አዩ፤ |
| 15. | የፈርዖንም አለቆች አዩአት፥ በፈርዖንም ፊት አመሰገኑአት፤ ሴቲቱንም ወደ ፈርዖን ቤት ወሰዱአት። |
| 16. | ለአብራምም ስለ እርስዋ መልካም አደረገለት፤ ለእርሱ በጎችም በሬዎችም አህዮችም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም ግመሎችም ነበሩት። |
| 17. | እግዚአብሔርም በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና የቤቱን ሰዎች በታላቅ መቅሠፍት መታ። |
| 18. | ፈርዖንም አብራምን ጠርቶ አለው። ይህ ያደረግህብኝ ምንድር ነው? እርስዋ ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልገለጥህልኝም? |
| 19. | ለምንስ። እኅቴ ናት አልህ? እኔ ሚስት ላደርጋት ወስጄአት ነበር። አሁንም ሚስትህ እነኋት፤ ይዘሃት ሂድ። |
| 20. | ፈርዖንም ሰዎቹን ስለ እርሱ አዘዘ፥ እርሱንም ሚስቱንም ከብቱንም ሁሉ ሸኙአቸው። a |
| ← Genesis (12/50) → |