Genesis (1/50) → |
1. | በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። |
2. | ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር። |
3. | እግዚአብሔርም። ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ። |
4. | እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ እግዚብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ። |
5. | እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንድ ቀን። |
6. | እግዚአብሔርም። በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል አለ። |
7. | እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፥ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ፤ እንዲሁም ሆነ። |
8. | እግዚአብሔር ጠፈርን ሰማይ ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሁለተኛ ቀን። |
9. | እግዚአብሔርም። ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ እንዲሁም ሆነ። |
10. | እግዚአብሔርም የብሱን ምድር ብሎ ጠራው፤ የውኃ መከማቻውንም ባሕር አለው፤ እግዚእብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። |
11. | እግዚአብሔርም። ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ፤ እንዲሁም ሆነ። |
12. | ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። |
13. | ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሦስተኛ ቀን። |
14. | እግዚአብሔርም አለ። ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤ |
15. | በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ። |
16. | እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን፤ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ። |
17. | እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፤ |
18. | በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። |
19. | ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን። |
20. | እግዚአብሔርም አለ። ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ። |
21. | እግዚአብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፥ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፥ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። |
22. | እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ባረካቸው። ብዙ ተባዙም የባሕርንም ውኃ ሙሉአት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ። |
23. | ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አምስተኛ ቀን። |
24. | እግዚአብሔርም አለ። ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፥ ታውጣ፤ እንዲሁም ሆነ። |
25. | እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፥ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፥ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። |
26. | እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። |
27. | እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። |
28. | እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው። ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። |
29. | እግዚአብሔርም አለ። እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ፤ |
30. | ለምድርም አራዊት ሁሉ፥ ለሰማይም ወፎች ሁሉ፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላቸው፤ እንዲሁም ሆነ። |
31. | እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን። |
Genesis (1/50) → |