← Galatians (4/6) → |
1. | ነገር ግን እላለሁ፥ ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ምንም የሁሉ ጌታ ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም፥ |
2. | ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው። |
3. | እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤ |
4. | ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ |
5. | እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። |
6. | ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። |
7. | ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ። |
8. | ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤ |
9. | አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን? |
10. | ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ። |
11. | ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ። |
12. | ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ሆኜአለሁና። እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ። አንዳችም አልበደላችሁኝም። |
13. | በመጀመሪያ ወንጌልን በሰበክሁላችሁ ጊዜ ከሥጋ ድካም የተነሣ እንደ ነበረ ታውቃላችሁ፥ |
14. | በሥጋዬም ፈተና የሆነባችሁን ነገር አልናቃችሁትምና አልተጸየፋችሁትም ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ አዎን እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ። |
15. | እንግዲህ ደስ ማሰኘታችሁ ወዴት አለ? ቢቻልስ ዓይኖቻችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ። |
16. | እንኪያስ እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን? |
17. | በብርቱ ይፈልጉአችኋል፥ ለመልካም አይደለም ነገር ግን በብርቱ ትፈልጉአቸው ዘንድ በውጭ ሊያስቀሩአችሁ ይወዳሉ። |
18. | ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ በምኖርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ በመልካም ነገር ተፈላጊ ብትሆኑ መልካም ነው። |
19. | ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል። |
20. | ስለ እናንተ አመነታለሁና አሁን በእናንተ ዘንድ ሆኜ ድምፄን ልለውጥ በወደድሁ። |
21. | እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፥ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ። |
22. | አንዱ ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት ተጽፎአልና። |
23. | ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአል፥ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዶአል። |
24. | ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት። |
25. | ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና። |
26. | ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት። |
27. | አንቺ የማትወልጅ መካን፥ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፥ እልል በዪና ጩኺ፤ ባል ካላቱ ይልቅ የብቸኛይቱ ልጆች በዝተዋልና ተብሎ ተጽፎአል። |
28. | እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን። |
29. | ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። |
30. | ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት። |
31. | ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም። |
← Galatians (4/6) → |