← Ezra (6/10) → |
1. | በዚያ ጊዜም ንጉሡ ዳርዮስ መዛግብት ባሉበት በባቢሎን ቤተ መጻሕፍት እንዲመረመር አዘዘ። |
2. | በሜዶን አውራጃ ባለው አሕምታ በሚባል ከተማ በንጉሡ ቤት ውስጥ አንድ ጥቅልል ተገኘ፥ በውስጡም ይህ ነገር ለመታሰቢያ ተጽፎ ነበር። |
3. | በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ እንዲህ ብሎ አዘዘ፤ በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት፥ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ፥ ይህ ቤት ይሠራ፥ በጽኑም ይመሥረት፤ ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድሳ ክንድ ይሁን። |
4. | በሦስት ተራ ታላላቅ ድንጋይ፥ በአንድ ተራ እንጨት ይደረግ፤ ውጪውም ከንጉሡ ቤት ይሰጥ። |
5. | ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው መቅደስ ወስዶ ወደ ባቢሎን ያመጣው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃ ይመለስ፤ በኢየሩሳሌምም ወዳለው መቅደስ ወደ ስፍራው ይወሰድ፥ በእግዚአብሔር ቤት ይኑር። |
6. | አሁንም አንተ በወንዝ ማዶ ያለኸው የአገሩ ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ በወንዝ ማዶም ያሉ ተባባሪዎቻችሁ አፈርስካውያን፥ ከዚያ ራቁ፤ |
7. | ይህም የእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ ተዉ፤ የአይሁድም አለቃና የአይሁድም ሽማግሌዎች ይህን የእግዚአብሔርን ቤት በስፍራው ይሠሩ ዘንድ ተዉአቸው። |
8. | ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ ለአይሁድ ሽማግሌዎች የምታደርጉትን፥ በወንዝ ማዶ ካለው አገር ከሚመጣው ግብር ከንጉሡ ገንዘብ ለእነዚህ ሰዎች ወጪውን በትጋት እንድትሰጡአቸው ሥራም እንዳታስፈቱአቸው አዝዣለሁ። |
9. | ለሰማይ አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያስፈልገውን፥ ወይፈኖችና አውራ በጎች ጠቦቶችም፥ በኢየሩሳሌምም እንዳሉ እንደ ካህናቱ ቃል ስንዴና ጨው የወይን ጠጅና ዘይት ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ ስጡአቸው። |
10. | ይኸውም ለሰማይ አምላክ ጣፋጭ ሽቱ የሆነውን መሥዋዕት ያቀረቡ ዘንድ ለንጉሡና ለልጆቹም ዕድሜ ይጸልዩ ዘንድ ነው። |
11. | ይህንም ትእዛዝ የሚለውጥ ሁሉ፥ ምሰሶው ከቤቱ ተነቅሎ እርሱ ይሰቀልበት፤ ቤቱም የጉድፍ መጣያ ይደረግ ብዬ አዝዣለሁ። |
12. | ስሙንም በዚያ ያኖረው አምላክ ይህን ይለውጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤት ያፈርሱት ዘንድ እጃቸውን የሚዘረጉትን ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ ያጥፋ። እኔ ዳርዮስ ይህን አዝዣለሁ፤ በትጋት ይፈጸም። |
13. | ንጉሡም ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ በዚያን ጊዜ በወንዝ ማዶ ያለ ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ ተባባሪዎቻቸውም እንዲሁ ተግተው አደረጉ። |
14. | የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት ሠሩ ተከናወነላቸውም። እንደ እስራኤልም አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ፋርስም ነገሥታት እንደ ቂሮስና እንደ ዳርዮስ እንደ አርጤክስስም ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። |
15. | ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ። |
16. | የእስራኤልም ልጆች፥ ካህናትና ሌዋውያን የቀሩትም ምርኮኞች፥ የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ቅዳሴ በደስታ አደረጉ። |
17. | በዚህም በእግዚአብሔር ቤት ቅዳሴ መቶ ወይፈኖችና ሁለት መቶ አውራ በጎች አራት መቶም ጠቦቶች አቀረቡ ፤ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ አሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። |
18. | በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈው በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕርጋቸው ሌዋውያኑም በየክፍላቸው አቆሙ። |
19. | ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አደረጉ። |
20. | ካህናቱና ሌዋውያኑም አንድ ሆነው ነጽተው ነበር፤ ሁሉም ንጹሐን ነበሩ፤ ለምርኮኞቹም ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸውም ለካህናቱ፥ ለራሳቸውም ፋሲካውን አረዱ። |
21. | ከምርኮም ተመልሰው የመጡት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኵሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ በሉ፤ |
22. | እግዚአብሔር ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት እጃቸውን ያጸና ዘንድ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ። |
← Ezra (6/10) → |