Ezra (4/10)  

1. የይሁዳና የብንያምም ጠላቶች ምርኮኞቹ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መቅደስ እንደ ሠሩ ሰሙ።
2. ወደ ዘሩባቤልና ወደ አባቶች ቤቶች አለቆች ቀርበው። የአሦር ንጉሥ አስራዶን ወደዚህ ካመጣን ቀን ጀምሮ ለአምላካችሁ እንሠዋለንና፥ እንደ እናንተም እንፈልገዋለንና ከእናንተ ጋር እንሥራ አሉአቸው።
3. ዘሩባቤልና ኢያሱም የቀሩትም የእስራኤል አባቶች ቤቶች አለቆች። የአምላካችንን ቤት መሥራት ለእኛና ለእናንተ አይደለም፤ እኛ ለብቻችን ግን የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዳዘዘን ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት እንሠራለን አሉአቸው።
4. የምድሩም ሕዝብ የይሁዳን ሕዝብ እጅ ያደክሙ ነበር፥ እንዳይሠሩም አስፈራሩአቸው፥
5. ምክራቸውንም ያፈርሱ ዘንድ በፋርሱ ንጉሥ በቂሮስ ዘመን ሁሉ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት ድረስ መካሪዎችን ገዙባቸው።
6. በአርጤክስስም መንግሥት፥ በመንግሥቱም በመጀመሪያ ዘመን፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ላይ የክስ ነገር ጻፉ።
7. በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፥ ሚትሪዳጡ፥ ጣብኤል ተባባሪዎቹም ለፋርስ ንጉሥ ለአርጤክስስ ጻፉ፤ ደብዳቤውም በሶርያ ፊደልና በሶርያ ቋንቋ ተጽፎ ነበር።
8. አዛዡ ሬሁም ጸሐፊውም ሲምሳይ በኢየሩሳሌም ላይ ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ።
9. አዛዡ ሬሁም ጸሐፊውም ሲምሳይ የቀሩትም ተባባሪዎቻቸው፥ ዲናውያን፥ አፈርሳትካውያን፥ ጠርፈላውያን፥ አፈርሳውያን፥ አርካውያን፥ ባቢሎናውያን፥ ሱስናካውያን፥ ዴሐውያን፥ ኤላማውያን፥
10. ታላቁና ኃይለኛው አስናፈር ያፈለሳቸው በሰማርያና በወንዝ ማዶ ያኖራቸው የቀሩትም አሕዛብ ደብዳቤውን ጻፉ።
11. ለንጉሡ ለአርጤክስስ የላኩት የደብዳቤ ግልባጭ ይህ ነው። በወንዝ ማዶ ያሉት ሰዎች ባሪያዎችህ፤
12. አሁንም ከአንተ ዘንድ የወጡ አይሁድ ወደ እኛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ መጡ ንጉሡ ይወቅ፤ ዓመፀኛይቱንና እጅግም የከፋቺቱን ከተማ ይሠራሉ፥ ቅጥርዋንም ያድሳሉ፥ መሠረትዋንም ጠገኑ።
13. አሁንም ይህች ከተማ የተሠራች እንደ ሆነ፥ ቅጥርዋም የታደሰ እንደ ሆነ፥ ግብርና ቀረጥ መጥንም እንዳይሰጡ፥ የንጉሡም ግቢው እንዲጐድል ንጉሡ ይወቅ።
14. የንጉሡንም ጨው እንበላለንና፥ ንጉሡንም ሲያቃልሉት ማየት አይገባንምና ስለዚህ ልከን ለንጉሡ አስታውቀናል፤
15. በአባቶችህ ታሪክ መጽሐፍ ምርመራ ይደረግ፤ በዚያም በታሪክ መጽሐፍ ይህች ከተማ ዓመፀኛ እንደ ሆነች፥ ነገሥታትንና አውራጃዎችንም እንደ ጐዳች፥ ከጥንቱም ሽፍትነት በእርስዋ እንደ ተጀመረ ታገኛለህ፥ ታውቃለህም፤ ስለዚህም ይህች ከተማ ፈርሳ ነበር።
16. ይህችም ከተማ የተሠራች እንደ ሆነ፥ ቅጥርዋም የታደሰ እንደ ሆነ፥ በወንዝ ማዶ ክፍል እንደሌለህ ለንጉሡ እናስታውቃለን።
17. ንጉሡም ለአዛዡ ለሬሁም፥ ለጸሐፊውም ለሲምሳይ፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶም ለተቀመጡ ለቀሩት ተባባሪዎቻቸው እንዲህ የሚለውን መልስ ላከ።
18. ሰላም፤ አሁንም ወደ እኛ የላካችሁት ደብዳቤ በፊቴ ተተርጕሞ ተነበበ።
19. እኔም አዝዣለሁ፥ ተመረመረም፤ ይህችም ከተማ ከጥንት ጀምራ በነገሥታት ላይ ዓመፀኛ እንደ ነበረች፥ በእርስዋም ዓመፅና ሽፍትነት እንደ ተደረገ ተገኘ።
20. በኢየሩሳሌምም እጅግ ኃያላን ነገሥታት ነበሩ፥ በወንዝም ማዶ ያለውን አገር ሁሉ ይገዙ ነበር፤ ግብርንና ቀረጥን መጥንንም ይቀበሉ ነበር።
21. አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲተዉ፥ እኔም እስካዝዝ ድረስ ይህች ከተማ እንዳትሠራ ትእዛዝ ስጡ።
22. ቸልም እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ ለነገሥታቱ ጉዳትና ጥፋት እየበዛ ስለ ምን ይሄዳል?
23. የንጉሡም የአርጤክስስ ደብዳቤ ግልባጭ በሬሁምና በጸሐፊው በሲምሳይ በተባባሪዎቻቸውም ፊት በተነበበ ጊዜ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አይሁድ ሄዱ፤ በግድና በኃይልም አስተዉአቸው።
24. በዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ቀረ፤ እስከ ፋርስም ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ተጓጐለ።

  Ezra (4/10)