← Ezra (3/10) → |
1. | ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ፥ የእስራኤልም ልጆች በከተሞቻቸው ሳሉ፥ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። |
2. | የኢዮሴዴቅም ልጅ ኢያሱ፥ ወንድሞቹም ካህናቱ፥ የሰላትያልም ልጅ ዘሩባቤል ወንድሞቹም ተነሥተው በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ ሠሩ። |
3. | በአገሩም ካሉት አሕዛብ ፈርተው ነበርና መሠዊያውን በስፍራው ላይ አስቀመጡት፥ በጥዋትና በማታም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡበት። |
4. | እንደ ተጻፈውም የዳስ በዓል አደረጉ፤ እንደ ሥርዓቱም ለየዕለቱ የተገባውን የየዕለቱን የሚቃጠል መሥዋዕት በቍጥር አቀረቡ። |
5. | ከዚያም በኋላ ዘወትር የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የመባቻውንም መሥዋዕት፥ የተቀደሱትንም የእግዚአብሔር በዓላት ሁሉ መሥዋዕት፥ ሰውም ሁሉ ለእግዚአብሔር በፈቃድ የሰጠውን ቍርባን አቀረቡ። |
6. | በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ፤ የእግዚአብሔር መቅደስ ገና አልተመሠረተም ነበር። |
7. | ለጠራቢዎችና ለአናጢዎችም ገንዘብ ሰጡ፤ የፋርስም ንጉሥ ቂሮስ እንደ ፈቀደላቸው የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ በባሕር ወደ ኢዮጴ ያመጡ ዘንድ ለሲዶናና ለጢሮስ ሰዎች መብልና መጠጥ ዘይትም ሰጡ። |
8. | በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፥ የኢዩሴዴቅም ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ወንድሞቻቸው ካህናትና ሌዋውያን፥ ወደ ኢየሩሳሌምም የተመለሱት ምርኮኞች ሁሉ ጀመሩ፤ ሌዋውያንንም ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ እንዲያሠሩት ሾሙአቸው። |
9. | ኢያሱም ልጆቹም ወንድሞቹም፥ የይሁዳም ልጆች ቀድምኤልና ልጆቹ፥ የኤንሐዳድም ልጆች፥ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን ያሠሩ ዘንድ በአንድነት ቆሙ። |
10. | አናጢዎቹም የእግዚአብሔርን መቅደስ በመሠረቱ ጊዜ ካህናቱ ልብሳቸውን ለብሰው መለከቱን ይዘው፥ የአሳፍም ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው እንደ እስራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት ሥርዓት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ። |
11. | ደግሞ። ቸር ነውና፥ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እያሉ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑና እያከበሩ እርስ በእርሳቸው ያስተዛዝሉ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ቤት ስለ ተመሠረተ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በታላቅ ድምፅ እልል አሉ። |
12. | የፊተኛውን ቤት ያዩ ሽማግሌዎች የሆኑ ብዙ ካህናትና ሌዋውያን የአባቶችም ቤቶች አለቆች ግን ይህ መቅደስ በፊታቸው በተመሠረተ ጊዜ በታላቅ ድምፅ ያለቅሱ ነበር፤ ብዙ ሰዎችም በደስታ ይጮኹ ነበር፤ |
13. | ደስ ብሎአቸው የሚጮኹትን ድምፅ ከሕዝቡ ልቅሶ ድምፅ መለየት የሚችል አልነበረም፤ ሕዝቡም በታላቅ ድምፅ ይጮኽ ነበር፥ ድምፁም ከሩቅ ይሰማ ነበር። |
← Ezra (3/10) → |