| Ezra (1/10) → |
| 1. | በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አድርጎ እንዲህ አለ። |
| 2. | የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል። የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ |
| 3. | ከሕዝቡ ሁሉ በእንናተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፥ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ፤ |
| 4. | በሚኖርበትም ስፍራ ሁሉ ለቀረው ሰው የአገሩ ሰዎች በብርና በወርቅ በዕቃም በእንስሳም ይርዱት፤ ይህም በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ከሚያቀርቡት ሌላ ይሁን። |
| 5. | የይሁዳና የብንያም የአባቶች ቤቶች አለቆችም፥ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ይወጡ ዘንድ እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው ሁሉ ተነሡ። |
| 6. | በዙሪያቸውም ያሉ ሁሉ በፈቃዳቸው ካቀረቡት ሁሉ ሌላ በብር ዕቃና በወርቅ በገንዘቦችና በእንስሶች በሌላም ስጦታ አገዙአቸው። |
| 7. | ንጉሡ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች አወጣ። |
| 8. | የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም በመዝገቡ ላይ በነበረው በሚትሪዳጡ እጅ አወጣቸው፥ ለይሁዳም መስፍን ለሰሳብሳር ቈጠራቸው። |
| 9. | ቍጥራቸውም ይህ ነው፤ ሠላሳ የወርቅ አንድ ሺህም የብር ሰሐኖች፥ ሀያ ዘጠኝም ቢላዎች፥ |
| 10. | ሠላሳ የወርቅ ደካዎች፥ አራት መቶ አሥርም ሌላ ዓይነት የብር ደካዎች፥ አንድ ሺህም ሌላ ዕቃ ነበረ። |
| 11. | የወርቁና የብሩ ዕቃዎች ሁሉ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ፤ እነዚህንም ሁሉ ሰሳብሳር ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ ምርኮኞቹ ጋር ወሰደ። |
| Ezra (1/10) → |