| ← Ezekiel (7/48) → |
| 1. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
| 2. | አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል። ፍጻሜ፥ በምድሪቱ በአራቱ ማዕዘን ላይ ፍጻሜ ደርሶአል። |
| 3. | አሁን ፍጻሜ በአንቺ ላይ ነው፥ ቍጣዬንም እሰድድብሻለሁ፥ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፥ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ። |
| 4. | ዓይኔም አይራራልሽም እኔም አላዝንም፤ መንገድሽንም አመጣብሻለሁ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ይሆናል፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። |
| 5. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ክፉ ነገር፥ አንድ ክፉ ነገር፥ እነሆ፥ ይመጣል። |
| 6. | ፍጻሜ መጥቶአል፥ ፍጻሜ መጥቶአል፥ ነቅቶብሻል፤ እነሆ፥ ደርሶአል። |
| 7. | በምድር የምትቀመጥ ሆይ፥ ተራህ ደርሶአል፥ ጊዜ መጥቶአል፥ ቀን ቀርቦአል፤ የሽብር ቀን ነው እንጂ በተራራ ላይ ያለ እልልታ አይደለም። |
| 8. | አሁን በቅርብ መዓቴን አፈስስብሻለሁ፥ ቍጣዬንም እፈጽምብሻለሁ፥ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፥ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ። |
| 9. | ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም፤ እንደ መንገድሽም መጠን አመጣብሻለሁ፥ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ይሆናል፥ እኔም እግዚአብሔር የምቀሥፍ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። |
| 10. | እነሆ ቀኑ፥ እነሆ፥ መጥቶአል፤ ተራህ ወጥቶአል፤ ብትር አብቦአል፥ ትዕቢትም አጅብጅፎአል። |
| 11. | ግፍ ወደ ክፋት ብትር ተነስቶአል፤ ከእነርሱና ከብዛታቸው ከሀብታቸውም ምንም አይቀርም፥ የሚያለቅስላቸውም የለም። |
| 12. | ጊዜው መጥቶአል፥ ቀኑ ቀርቦአል፤ መዓት በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና የሚገዛ ደስ አይበለው የሚሸጥም አያልቅስ። |
| 13. | የሚሸጥ ወደሸጠው ነገር አይመለስም፥ ሰውም በነፍሱ ኃጢአት አይጸናም። |
| 14. | መለከቱን ነፍተዋል ሁሉንም አዘጋጅተዋል፤ ነገር ግን መዓቴ በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና ወደ ሰልፍ የሚሄድ የለም። |
| 15. | ሰይፍ በውጭ ቸነፈርና ራብ በውስጥ አለ፤ በሜዳ ያለው በሰይፍ ይሞታል፥ በከተማም ያለውን ቸነፈርና ራብ ይፈጁታል። |
| 16. | ከእነርሱም የሚሸሹ ይድናሉ በተራራም ላይ ይሆናሉ፤ እኔም በኃጢአታቸው ሁሉን እገድላለሁ። |
| 17. | እጅ ሁሉ ትደክማለች ጕልበትም ሁሉ እንደ ውኃ ትቀልጣለች። |
| 18. | ማቅም ይለብሳሉ ድንጋጤም ይሸፍናቸዋል፤ በፊትም ሁሉ ላይ እፈረት ይሆናል፥ ራሳቸውንም ሁሉ ይነጩታል። |
| 19. | ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ ወርቃቸውም እንደ ጕድፍ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ያድናቸው ዘንድ አይችልም። እርሱ የኃጢአታቸው ዕንቅፋት ሆኖአልና ሰውነታቸውን አያጠግቡም ሆዳቸውንም አይሞሉም። |
| 20. | የክብሩንም ጌጥ ወደ ትዕቢት ለወጡ፥ የርኵስነታቸውንም ምስሎች አደረጉባት፤ ስለዚህ እኔ በእነርሱ ዘንድ ርኩስ አድርጌአታለሁ። |
| 21. | በባዕድም እጅ ለንጥቂያ፥ በምድር ኃጢአተኞችም እጅ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እነርሱም ያረክሱአታል። |
| 22. | ፊቴን ከእነርሱ ዘንድ እመልሳለሁ፥ ምሥጢሬንም ያረክሳሉ፤ ወንበዴዎችም ይገቡባታል ያረክሱአትማል። |
| 23. | ምድር ደም ባመጣው በደል፥ ከተማም በግፍ ተሞልታለችና ሰንሰለት ሥራ። |
| 24. | ከአሕዛብ ዘንድ ከሁሉ የሚከፉትን አመጣለሁ ቤቶቻቸውንም ይወርሳሉ፤ የኃያላንንም ትዕቢት አጠፋለሁ፥ መቅደሶቻቸውም ይረክሳሉ። |
| 25. | ጥፋት መጥቶአል፤ ሰላምም ይሻሉ እርሱም አይገኝም። |
| 26. | ድንጋጤ በድንጋጤ ላይ ይመጣል፥ ወሬም ወሬውን ይከተላል፥ ከነቢዩም ዘንድ ራዕይን ይሻሉ፤ ከካህኑም ዘንድ ትምህርት፥ ከሽማግሌዎችም ዘንድ ምክር ይጠፋል። |
| 27. | ንጉሡም ያለቅሳል፥ አለቃም ውርደትን ይለብሳል፥ የምድርም ሕዝብ እጅ ትንቀጠቀጣለች፤ እንደ መንገዳቸውም መጠን አደርግባቸዋለሁ፥ በፍርዳቸውም መጠን እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። |
| ← Ezekiel (7/48) → |