Ezekiel (5/48)  

1. አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የተሳለን ጐራዴ ውሰድ፥ እንደ ጢም መላጫ ወደ አንተ ትወስደዋለህ፥ ራስህንና ጢምህንም ትላጭበታለህ፤ ሚዛንንም ውሰድ ጠጕሩንም ትከፋፍላለህ።
2. የመከበብም ወራት በተፈጸመ ጊዜ በከተማይቱ መካከል ሢሶውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ሢሶውንም ወስደህ ዙሪያውን በጐራዴ ትመታለህ፥ ሢሶውንም ወደ ነፋስ ትበትናለህ እኔም በኋላቸው ጐራዴ እመዝዛለሁ።
3. ከዚያም በጥቂቱ ውሰድ በመጐናጸፊያህም ጫፍ ቋጥራቸው።
4. ከእነርሱም ደግሞ ወስደህ በእሳት ውስጥ ትጥላለህ በእሳትም ታቃጥላቸዋለህ፤ ከዚያም በእስራኤል ቤት ሁሉ ላይ እሳት ትወጣለች።
5. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህች ኢየሩሳሌም ናት፤ በአሕዛብም መካከል አድርጌአታለሁ፥ አገሮችም በዙሪያዋ አሉ።
6. እርስዋም ከአሕዛብ ይልቅ ፍርዴን በኃጢአት ለወጠች በዙሪያዋም ካሉ አገሮች ሁሉ ይልቅ ትእዛዜን ተላለፈች፤ ፍርዴን ጥለዋልና፥ በትእዛዜም አልሄዱምና።
7. ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዙሪያችሁ ላሉት አሕዛብ ሰበብ ሆናችኋልና፥ በትእዛዜም አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አልጠበቃችሁምና፥ በዙሪያችሁም እንዳሉ እንደ አሕዛብ ፍርድ እንኳ አላደረጋችሁምና
8. ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ነኝ፥ አሕዛብም እያዩ ፍርድን በመካከልሽ አደርጋለሁ።
9. ስለ ርኵሰትሽም ሁሉ ያልሠራሁትን እርሱንም የሚመስል ደግሞ የማልሠራውን ነገር እሠራብሻለሁ።
10. ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፤ ፍርድንም አደርግብሻለሁ ከአንቺም የቀረውን ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ።
11. ስለዚህ፥ እኔ ሕያው ነኝና በእድፍሽና በርኵሰትሽ መቅደሴን ስላረከስሽ፥ ስለዚህ በእውነት እኔ አሳንስሻለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም።
12. ከአንቺም ሢሶው በቸነፈር ይሞታል፥ በመካከልሽም በራብ ያልቃል፤ ሢሶውም በዙሪያሽ በሰይፍ ይወድቃል፤ ሢሶውንም ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ።
13. ቍጣዬም ይፈጸማል መዓቴንም እጨርሳለሁ እጽናናማለሁ፥ መዓቴንም በፈጸምሁባቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር በቅንዓቴ እንደ ተናገርሁ ያውቃሉ።
14. በዙሪያሽም ባሉ በአሕዛብ መካከል በሚያልፉም ሁሉ ፊት ባድማና መሰደቢያ አደርግሻለሁ።
15. በቍጣና በመዓት፥ በመዓትም ዘለፋ ፍርድን ባደረግሁብሽ ጊዜ በዙሪያሽ ላሉ አሕዛብ መሰደቢያና መተረቻ፥ ተግሣጽና መደነቂያ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።
16. ለማጥፋትም የሆነውን፥ አጠፋችሁም ዘንድ የምሰድደውን የራብ ፍላጻ በላያችሁ በሰደድሁ ጊዜ፥ ራብን እጨምርባችኋለሁ፥ የእንጀራችሁንም በትር እሰብራለሁ።
17. ራብንና ክፉዎችን አራዊት እሰድድባችኋለሁ፥ ልጆቻችሁንም ያጠፋሉ፤ ቸነፈርና ደምም በአንቺ ዘንድ ያልፋሉ፤ ሰይፍንም አመጣብሻለሁ። እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

  Ezekiel (5/48)