← Ezekiel (47/48) → |
1. | ወደ መቅደሱም መዝጊያ መለሰኝ፤ እነሆም፥ ውኃ ከቤቱ መድረክ በታች ወደ ምሥራቅ ይወጣ ነበር፥ የቤቱ ፊት ወደ ምሥራቅ ይመለከት ነበርና፤ ውኃውም ከቤቱ ከቀኝ ወገን በታች በመሠዊያው በደቡብ በኩል ይወርድ ነበር። |
2. | በሰሜኑም በር በኩል አወጣኝ፤ በስተ ውጭ ባለው መንገድ፥ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከት በስተ ውጭ ወዳለው በር አዞረኝ፤ እነሆም፥ ውኃው በቀኙ ወገን ይፈስስ ነበር። |
3. | ሰውዬውም ገመዱን በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ ወጣ አንድ ሺህም ክንድ ለካ፥ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃም እስከ ቍርጭምጭሚት ደረሰ። |
4. | ደግሞ አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃውም እስከ ጕልበት ደረሰ። ደግሞም አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃውም እስከ ወገብ ደረሰ። |
5. | ደግሞ አንድ ሺህ ለካ ልሻገረውም የማልችለው ወንዝ ሆነ፤ ውኃውም ጥልቅ ነበረ፥ የሚዋኝበትም ውኃ ነበረ፤ ሰው ሊሻገረው የማይችለው ወንዝ ነበረ። |
6. | እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ አይተሃልን? አለኝ። አመጣኝም፥ ወደ ወንዙም ዳር መለሰኝ። |
7. | በተመለስሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ እጅግ ብዙ ዛፎች ነበሩ። |
8. | እርሱም እንዲህ አለኝ። ይህ ውኃ ወደ ምሥራቅ ምድር ይወጣል ወደ ዓረባም ይወርዳል ወደ ባሕሩም ይገባል፤ ወደ ባሕሩም ወደ ረከሰው ውኃ በገባ ጊዜ ውኃው ይፈወሳል። |
9. | ሕያው ነፍስ ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ ወንዙ በመጣበት ስፍራ ሁሉ በሕይወት ይኖራል፤ ይህም ውኃ በዚያ ስለ ደረሰ ዓሣዎች እጅግ ይበዛሉ፤ የባሕሩም ውኃ ይፈወሳል፥ ወንዙም በሚመጣበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል። |
10. | አጥማጆችም በዚያ ይቆማሉ፤ ከዓይንጋዲ ጀምሮ እስከ ዓይንኤግላይም ድረስ መረብ መዘርጊያ ይሆናል፤ ዓሣዎችም እንደ ታላቁ ባሕር ዓሣዎች በየወገናቸው እጅግ ይበዛሉ። |
11. | እረግረጉና እቋሪው ውኃ ግን ጨው እንደ ሆነ ይኖራል እንጂ አይፈወስም። |
12. | በወንዙም አጠገብ በዳሩ ላይ በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ሁሉ ይበቅላል፥ ቅጠሉም አይረግፍም ፍሬውም አይጐድልም፤ ውኃውም ከመቅደስ ይወጣልና በየወሩ ሁሉ የፍሬ በኵር ያገኛል፤ ፍሬውም ለመብል ቅጠሉም ለመድኃኒት ይሆናል። |
13. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ርስት አድርጋችሁ ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ምድሪቱን የምትከፍሉበት ድንበር ይህ ነው። ለዮሴፍ ሁለት እድል ፈንታ ይሆናል። |
14. | ለአባቶቻችሁ እሰጣቸው ዘንድ ምዬ ነበርና እናንተ እኩል አድርጋችሁ ተካፈሉት ይህችም ምድር ርስት ትሆናችኋለች። |
15. | የምድሪቱም ድንበር ይህ ነው። በሰሜኑ ወገን ከታላቁ ባሕር ጀምሮ በሔትሎን መንገድ ወደ ጽዳድ መግቢያ፤ |
16. | ሐማት፥ ቤሮታ፥ በደማስቆ ድንበርና በሐማት ድንበር መካከል ያለው ሲብራይም፥ በሐውራን ድንበር አጠገብ ያለው ሐጸርሃቲኮን። |
17. | ድንበሩ ከባሕሩ በደማስቆ ድንበር ላይ ያለው ሐጸርዔናን ይሆናል፥ በሰሜንም በኩል የሐማት ድንበር አለ። የሰሜኑ ድንበር ይህ ነው። |
18. | የምሥራቁም ድንበር በሐውራን በደማስቆና በገለዓድ በእስራኤልም ምድር መካከል ዮርዳኖስ ይሆናል። ከሰሜኑ ድንበር ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ባሕር እስከ ታማር ድረስ የምሥራቁ ድንበር ይህ ነው። |
19. | የደቡቡም ድንበር ከታማር ጀምሮ እስከ ሜርባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። የደቡቡ ድንበር ይህ ነው። |
20. | የምዕራቡም ድንበር ከደቡቡ ድንበር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ አንጻር ድረስ ታላቁ ባሕር ይሆናል። የምዕራቡ ድንበር ይህ ነው። |
21. | እንዲሁ ይህችን ምድር እንደ እስራኤል ነገዶች መጠን ለእናንተ ትካፈላላችሁ። |
22. | ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጡ በእናንተም መካከል ልጆችን ለሚወልዱ መጻተኞች ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ትካፈሉአታላችሁ፤ እነርሱም በእስራኤል ልጆች መካከል እንዳሉ የአገር ልጆች ይሆኑላችኋል፥ በእስራኤልም ነገዶች መካከል ከእናንተ ጋር ርስትን ይወርሳሉ። |
23. | መጻተኛውም በማናቸውም ነገድ መካከል ቢቀመጥ በዚያ ርስቱን ትሰጡታላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
← Ezekiel (47/48) → |