← Ezekiel (45/48) → |
1. | ርስትም አድርጋችሁ ምድርን በዕጣ በምታካፍሉበት ጊዜ ከምድር የተቀደሰውን የዕጣ ክፍል መባ አድርጋችሁ ወደ እግዚአብሔር ታቀርባላችሁ። ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም ሀያ ሺህ ክንድ ይሆናል፤ በዳርቻው ሁሉ ዙሪያውን የተቀደሰ ይሆናል። |
2. | ከእርሱም ርዝመቱ አምስት መቶ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ አራት ማዕዘን የሆነ ቦታ ለመቅደሱ ይሆናል፤ በዙሪያውም ባዶ ስፍራ የሚሆን አምሳ ክንድ ይሆናል። |
3. | ከዚያው ልክ ደግሞ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም አሥር ሺህ ክንድ የሆነ ስፍራ ትለካለህ፤ በእርሱም ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን የሆነ መቅደስ ይሆናል። |
4. | ከምድርም የተቀደሰ የዕጣ ክፍል ይሆናል፤ እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ለሚቀርቡ ለመቅደሱ አገልጋዮች ለካህናቱ ይሆናል፥ ለቤቶቻቸውም የሚሆን ስፍራ ለመቅደስም የሚሆን የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል። |
5. | ርዝመቱም ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም አሥር ሺህ የሆነ ዕፍራ ለቤቱ አገልጋዮች ለሌዋውያን ይሆናል፥ ለሚቀመጡባቸውም ከተሞች ለራሳቸውም የርስት ይዞታ ይሆናል። |
6. | ለከተማይቱም ይዞታ በተቀደሰው የዕጣ ክፍል መባ አጠገብ ወርዱ አምስት ሺህ ርዝመቱም ሀያ አምስት ሺህ የሆነውን ስፍራ ታደርጋላችሁ። እርሱም ለእስራኤል ቤት ሁሉ ይሆናል። |
7. | ለአለቃውም የሆነ የዕጣ ክፍል በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ አጠገብ በዚህና በዚያ ይሆናል፤ በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ ፊት በምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ በምሥራቅም በኩል ወደ ምሥራቅ ይሆናል፤ ርዝመቱም እንደ አንድ ነገድ ዕጣ ክፍል ሆኖ ከምድሩ ከምዕራቡ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ዳርቻ ድረስ ይሆናል። |
8. | ይህም በእስራኤል ዘንድ ይዞታ ይሆንለታል፥ አለቆቼም ለእስራኤል ቤት ምድሪቱን እንደ ነገዳቸው መጠን ይሰጡአቸዋል እንጂ ሕዝቤን ከእንግዲህ ወዲህ አያስጨንቋቸውም። |
9. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤል አለቆች ሆይ፥ ይብቃችሁ፤ ግፍንና ብዝበዛን አስወግዱ፥ ፍርድንና ጽድቅንም አድርጉ፤ ቅሚያችሁን ከሕዝቤ ላይ አርቁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
10. | እውነተኛ ሚዛን እውነተኛም የኢፍ መስፈሪያ እውነተኛውም የባዶስ መስፈሪያ ይሁንላችሁ። |
11. | የኢፍና የባዶስ መስፈሪያ አንድ ይሁን፤ የባዶስ መስፈሪያ የቆሮስ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል፥ የኢፍ መስፈሪያውም የቆሮስ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል ይሁን። መስፈሪያው እንደ ቆሮስ መስፈሪያ ይሁን። |
12. | ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ይሁን፤ ሀያ ሰቅል፥ ሀያ አምስት ሰቅል፥ አሥራ አምስት ሰቅል፥ ምናን ይሁንላችሁ። |
13. | የምታቀርቡት መባ ይህ ነው፤ ከአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ የኢፍ መስፈሪያ ስድስተኛ ክፍል፥ ከአንድም ቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የኢፍ መስፈሪያ ስድስተኛ ክፍል ትሰጣላችሁ። |
14. | የዘይቱም ደንብ፥ ከእያንዳንዱ የቆሮስ መስፈሪያ የባዶስን አሥረኛ ክፍል ትሰጣላችሁ፤ አሥር የባዶስ መስፈሪያ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ነውና። |
15. | ውኃም ካለበት ከእስራኤል ማሰማርያ ከመንጋው ከሁለቱ መቶ አንዱን የበግ ጠቦት ትሰጣላችሁ፤ ይህ ያስተሰርይላችሁ ዘንድ ለእህል ቍርባንና ለሚቃጠል መሥዋዕት ለደኅንነትም መሥዋዕት ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
16. | የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ይህን መባ ለእስራኤል አለቃ ይሰጣሉ። |
17. | በየበዓላቱም በየመባቻውም በየሰንበታቱም በእስራኤልም ቤት ዓመት በዓል ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን የመጠጡንም ቍርባን መስጠት በአለቃው ላይ ይሆናል፤ እርሱ ለእስራኤል ቤት ያስተሰርይ ዘንድ የኃጢአቱን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቀርባል። |
18. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ነውር የሌለበትን ወይፈን ውሰድ መቅደሱንም አንጻ። |
19. | ካህኑም ከኃጢአቱ መሥዋዕት ደም ወስዶ በመቅደሱ መቃኖችና በመሠዊያው እርከን በአራቱ ማዕዘን በውስጠኛውም አደባባይ በበሩ መቃኖች ላይ ይርጨው። |
20. | ከወሩም በሰባተኛው ቀን እንዲሁ አድርግ፥ ይኸውም ስለ ሳተውና ስላላወቀው ሁሉ ነው። እንዲሁም ስለ ቤቱ አስተስርዩ። |
21. | በመጀመሪያ ወር ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል ታደርጋላችሁ። እስከ ሰባት ቀንም ድረስ ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ። |
22. | በዚያም ቀን አለቃው ለራሱና ለአገሩ ሕዝብ ሁሉ የኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ያቅርብ። |
23. | በበዓሉም በሰባቱ ቀኖች የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ሰባቱን ቀኖች በየዕለቱ ነውር የሌለባቸውን ሰባት ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ያቅርብ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት በየዕለቱ አንድ አውራ ፍየል ያቅርብ። |
24. | ለአንድም ወይፈን አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአንድም አውራ በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአንድም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ለእህል ቍርባን ያቅርብ። |
25. | በሰባተኛውም ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን በበዓሉ ሰባት ቀኖች፥ የኃጢአቱን መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የእህሉንም ቍርባን ከዘይቱ ጋር እንዲሁ ያቅርብ። |
← Ezekiel (45/48) → |