Ezekiel (43/48)  

1. ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በር አመጣኝ።
2. እነሆም፥ የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ መንገድ መጣ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኆች ይተምም ነበር፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር ታበራ ነበር።
3. ያየሁትም ራእይ ከተማይቱን ለማጥፋት በመጣሁ ጊዜ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ ራእዩም በኮበር ወንዝ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ።
4. የእግዚአብሔርም ክብር ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር ወደ መቅደሱ ገባ።
5. መንፈሱም አነሣኝ ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አገባኝ፤ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ክብር መቅደሱን ሞልቶት ነበር።
6. በመቅደሱም ሆኖ የሚናገረኝን ሰማሁ፥ በአጠገቤም ሰው ቆሞ ነበር።
7. እንዲህም አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል ለዘላለም የምቀመጥበት የዙፋኔ ስፍራና የእግሬ ጫማ መረገጫ ይህ ነው። ዳግመኛም የእስራኤል ቤትና ነገሥታቶቻቸው በግልሙትናቸውና በከፍታዎቻቸው ባለው በነገሥታቶቻቸው ሬሳ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም፤
8. መድረካቸውን በመድረኬ አጠገብ፥ መቃናቸውንም በመቃኔ አጠገብ አድርገዋልና። በእኔና በእነርሱም መካከል ግንብ ብቻ ነበረ፤ በሠሩትም ርኵሰት ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለዚህ በቍጣዬ አጠፋኋቸው።
9. አሁንም ግልሙትናቸውንና የነገሥታቶቻቸውን ሬሳ ከእኔ ዘንድ ያርቁ፥ እኔም ለዘላለም በመካከላቸው አድራለሁ።
10. አንተም የሰው ልጅ፥ ከኃጢአታቸው የተነሣ ያፍሩ ዘንድ ለእስራኤል ወገን ይህን ቤት አሳያቸው አምሳያውንም ይለኩ።
11. ከሠሩትም ሥራ ሁሉ የተነሣ ቢያፍሩ፥ የቤቱን መልክና ምሳሌውን መውጫውንም መግቢያውንም ሥርዓቱንም ሕጉንም ሁሉ አስታውቃቸው፤ ሥርዓቱንና ሕጉን ሁሉ ይጠብቁ ዘንድ ያደርጉትም ዘንድ በፊታቸው ጻፈው።
12. የቤቱ ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ራስ ላይ ዳርቻው ሁሉ በዙሪያው ከሁሉ ይልቅ የተቀደስ ይሆናል። እነሆ፥ የቤቱ ሕግ ይህ ነው።
13. የመሠዊያውም ልክ በክንድ ይህ ነው፥ ክንዱም ክንድ ተጋት ነው። የመሠረቱም ቁመቱ አንድ ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፥ አንድ ስንዝርም ክፈፍ ዳር ዳሩን በዙሪያው አለ፤ የመሠዊያው መሠረት እንዲሁ ነው።
14. በመሬቱም ላይ ካለው መሠረት ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ሁለት ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፤ ከትንሹም እርከን ጀምሮ እስከ ትልቁ እርከን ድረስ አራት ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው።
15. ምድጃውም አራት ክንድ ነው፤ በምድጃውም ላይ አንድ ክንድ ወደ ላይ ከፍ የሚሉ አራት ቀንዶች አሉበት።
16. የምድጃውም ርዝመት አሥራ ሁለት ክንድ ወርዱም አሥራ ሁለት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው።
17. የእርከኑም ርዝመት አሥራ አራት ክንድ ወርዱም አሥራ አራት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው፤ በዙሪያውም ያለው ክፈፍ እኩል ክንድ ነው፥ መሠረቱም በዙሪያው አንድ ክንድ ነው፤ ደረጃዎቹም ወደ ምሥራቅ ይመለከታሉ።
18. እንዲህም አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ ደሙንም ይረጩበት ዘንድ በሚሠሩበት ቀን የመሠዊያው ሕግ ይህ ነው።
19. ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ለሚቀርቡ ከሳዶቅ ዘር ለሚሆኑ ለሌዋውያኑ ካህናት ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
20. ከደሙም ትወስዳለህ፥ በአራቱ ቀንዶቹም በእርከኑም በአራቱ ማዕዘን ላይ በዙሪያውም ባለው ክፈፍ ላይ ትረጨዋለህ፤ እንዲሁ ታነጻዋለህ ታስተሰርይለትማለህ።
21. ለኃጢአትም መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትወስዳለህ፥ በመቅደሱም ውጭ በቤቱ በታዘዘው ስፍራ ይቃጠላል።
22. በሁለተኛውም ቀን ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ነውር የሌለበትን አውራ ፍየል ታቀርባለህ፤ በወይፈኑም እንዳነጹት እንዲሁ መሠዊያውን ያነጹበታል።
23. ማንጻቱንም ከፈጸምህ በኋላ ነውር የሌለበትን ወይፈን ከመንጋውም የወጣውን ነውር የሌለበትን አውራ በግ ታቀርባለህ።
24. በእግዚአብሔርም ፊት ታቀርባቸዋለህ፥ ካህናቱም ጨው ይጨምሩባቸዋል፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር ያቀርቡአቸዋል።
25. ሰባት ቀንም በየዕለቱ ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ ፍየልን ታቀርባለህ፥ ነውርም የሌለባቸውን አንድ ወይፈን ከመንጋውም የወጣውን አንድ አውራ በግ ያቀርባሉ።
26. ሰባት ቀን ለመሠዊያው ያስተሰርያሉ ያነጹትማል፥ እንዲሁም ይቀድሱታል።
27. ቀኖቹንም በፈጸሙ ጊዜ በስምንተኛው ቀን ከዚያም በኋላ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን የደኅንነትንም መሥዋዕታችሁን በመሠዊያው ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

  Ezekiel (43/48)