| ← Ezekiel (37/48) → |
| 1. | የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ ነበረ እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ አጥንቶችም በሞሉባት ሸለቆ መካከል አኖረኝ። |
| 2. | በእነርሱም አንጻር በዙሪያቸው አሳለፈኝ፤ እነሆም፥ በሸለቆው ፊት እጅግ ብዙ ነበሩ፥ እነሆም፥ እጅግ ደርቀው ነበር። |
| 3. | እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን? አለኝ። እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁ። |
| 4. | እርሱም እንዲህ አለኝ። በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው። እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ። |
| 5. | ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ትንፋሽን አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ። |
| 6. | ጅማትም እሰጣችኋለሁ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። |
| 7. | እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፤ ስናገርም ድምፅ ሆነ፥ እነሆም፥ መናወጥ ሆነ፥ አጥንቶችም አጥንት ከአጥንት ጋር ተቀራረቡ። |
| 8. | እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ጅማት ነበረባቸው ሥጋም ወጣ ቁርበትም በላያቸው ተዘረጋ፥ ትንፋሽ ግን አልነበረባቸውም። |
| 9. | እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ እነዚህም የተገደሉት በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው በል አለኝ። |
| 10. | እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ ትንፋሽም ገባባቸው ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ። |
| 11. | እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች የእስራኤል ቤት ሁሉ ናቸው፤ እነሆ። አጥንቶቻችን ደርቀዋል ተስፋችንም ጠፍቶአል ፈጽመንም ተቈርጠናል ብለዋል። |
| 12. | ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ፥ መቃብራችሁን እከፍታለሁ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ፥ ወደ እስራኤልም ምድር አገባችኋለሁ። |
| 13. | ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። |
| 14. | መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁም አኖራችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ እንዳደረግሁም ታውቃላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። |
| 15. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
| 16. | አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ አንድ በትር ውሰድና። ለይሁዳና ለባልንጀሮቹ ለእስራኤል ልጆች ብለህ በላዩ ጻፍ፤ ሌላም በትር ውሰድና። የኤፍሬም በትር ለዮሴፍና ለባልንጀሮቹ ለእስራኤል ቤት ሁሉ ብለህ በላዩ ጻፍ። |
| 17. | አንድ በትርም እንዲሆኑ አንዱን ከሁለተኛው ጋር ለአንተ አጋጥም፥ በእጅህም ውስጥ አንድ ይሁኑ። |
| 18. | የሕዝብህም ልጆች። ይህ የምታደርገው ነገር ምን ማለት እንደሆነ አትነግረንምን? ብለው በተናገሩህ ጊዜ፥ |
| 19. | አንተ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በኤፍሬም እጅ ያለውን የዮሴፍን በትር ባልንጀሮቹንም የእስራኤልን ነገዶች እወስዳለሁ፥ ከእርሱም ከይሁዳ በትር ጋር አጋጥማቸዋለሁ አንድ በትርም አደርጋቸዋለሁ፥ በእጄም ውስጥ አንድ ይሆናሉ በላቸው። |
| 20. | የምትጽፍባቸውም በትሮች በዓይናቸው ፊት በእጅህ ውስጥ ይሆናሉ። |
| 21. | አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የእስራኤልን ልጆች ከሄዱባቸው ከአሕዛብ መካከል እወስዳለሁ ከስፍራም ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ |
| 22. | በምድርም ላይ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፥ አንድ ንጉሥም በሁላቸው ላይ ይነግሣል፤ ከዚያ ወዲያ ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፥ ከዚያ ወዲያም ሁለት መንግሥቶች ሆነው አይለዩም። |
| 23. | ከዚያ ወዲያም በጣዖቶቻቸውና በርኵሰታቸው በመተላለፋቸውም ሁሉ አይረክሱም፥ ኃጢአትም ከሠሩባት ዓመፅ ሁሉ አድናቸዋለሁ አነጻቸውማለሁ፤ ሕዝብም ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። |
| 24. | ባሪያዬም ዳዊት ንጉሥ ይሆናቸዋል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል፤ በፍርዴም ይሄዳሉ ትእዛዜንም ይጠብቃሉ ያደርጓትማል። |
| 25. | አባቶቻችሁም በኖሩበት ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድር ይኖራሉ፤ እነርሱና ልጆቻቸው የልጅ ልጆቻቸውም ለዘላለም ይኖሩባታል፤ ባሪያዬም ዳዊት ለዘላለም አለቃ ይሆናቸዋል። |
| 26. | የሰላምም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፥ የዘላለምም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፤ እኔም እባርካቸዋለሁ አበዛቸውማለሁ መቅደሴንም ለዘላለም በመካከላቸው አኖራለሁ። |
| 27. | ማደሪያዬም በላያቸው ላይ ይሆናል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። |
| 28. | መቅደሴም ለዘላለም በመካከላቸው በሆነ ጊዜ፥ እኔ እስራኤልን የምቀድሰው እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ። |
| ← Ezekiel (37/48) → |