| ← Ezekiel (35/48) → |
| 1. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
| 2. | የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሴይር ተራራ አድርግ፥ ትንቢትም ተናገርበት፥ |
| 3. | እንዲህም በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሴይር ተራራ ሆይ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ እጄንም እዘረጋብሃለሁ ባድማና ውድማም አደርግሃለሁ። |
| 4. | ከተሞችህንም አፈራርሳቸዋለሁ፥ አንተም ባድማ ትሆናለህ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ። |
| 5. | የዘላለም ጥል ስላለህ በመከራቸውም ጊዜ በኋለኛይቱ የኃጢአታቸው ቀጠሮ ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በሰይፍ እጅ ጥለሃቸዋልና |
| 6. | ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ለደም አሳልፌ እሰጥሃለሁ ደምም ያሳድድሃል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ደምን ስላልጠላህ ደም ያሳድድሃል። |
| 7. | የሴይርንም ተራራ ውድማ አደርገዋለሁ፥ የሚሄደውንና የሚመለሰውንም ከእርሱ አጠፋለሁ። |
| 8. | ተራሮቹንም በተገደሉት ሰዎች እሞላለሁ፤ በኮረብቶችህና በሸለቆችህ በፈሳሾችህም ሁሉ ላይ በሰይፍ የተገደሉት ሁሉ ይወድቃሉ። |
| 9. | ለዘላለምም ባድማ አደርግሃለሁ ከተሞችህም ሰው የማይኖርባቸው ይሆናሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። |
| 10. | እግዚአብሔርም በዚያ ሳለ፥ አንተ። እነዚህ ሁለቱ ሕዝቦች እነዚህም ሁለቱ አገሮች ለእኔ ይሆናሉ እኛም እንወርሳቸዋለን ብለሃልና |
| 11. | ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና እንደ ቍጣህ መጠን እነርሱንም ጠልተህ እንዳደረግኸው እንደ ቅንዓትህ መጠን እኔ እሠራለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በፈረድሁብህም ጊዜ በእነርሱ ዘንድ የታወቅሁ እሆናለሁ። |
| 12. | አንተም። ፈርሰዋል መብልም ሆነው ለእኛ ተሰጥተዋል ብለህ በእስራኤል ተራሮች ላይ የተናገርኸውን ስድብ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሰማሁት ታውቃለህ። |
| 13. | በአፋችሁም ተመካችሁብኝ፥ ቃላችሁንም አበዛችሁብኝ፤ እኔም ሰምቼዋለሁ። |
| 14. | ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ምድር ሁሉ ደስ ሲላት አንተን ባድማ አደርግሃለሁ። |
| 15. | የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ ስለ ሆነ በላዩ ደስ እንዳለህ፥ እንዲሁ አደርግብሃለሁ፤ የሴይር ተራራ ሆይ፥ አንተና ኤዶምያስ ሁሉ ሁለንተናውም ባድማ ትሆናላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። |
| ← Ezekiel (35/48) → |