| ← Ezekiel (34/48) → |
| 1. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
| 2. | የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞችንም እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? |
| 3. | ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም። |
| 4. | የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው። |
| 5. | እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም። |
| 6. | በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሻም የሚፈልግም አልነበረም። |
| 7. | ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ |
| 8. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና |
| 9. | ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ |
| 10. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያሰማሩም፤ በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም። |
| 11. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልግማለሁ። |
| 12. | እረኛ በተበተኑት በጎች መካከል ባለ ጊዜ መንጋውን እንደሚፈልግ፥ እንዲሁ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ በደመናና በጨለማ ቀን ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ። |
| 13. | ከአሕዛብም ዘንድ አወጣቸዋለሁ ከአገሮችም እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ አገራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በፈሳሾችም አጠገብ በምድርም ላይ ሰዎች በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ። |
| 14. | በመልካም ማሰማርያ እሰማራቸዋለሁ ጕረኖአቸውም በረጅሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፤ በዚያ በመልካም ጕረኖ ውስጥ ይመሰጋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ ማሰማርያ ይሰማራሉ። |
| 15. | እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ አስመስጋቸውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
| 16. | የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውንም አጠፋለሁ፤ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ። |
| 17. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እናንተም መንጋዬ ሆይ፥ እነሆ፥ በበግና በበግ መካከል፥ በአውራ በግና በአውራ ፍየልም መካከል፥ እፈርዳለሁ። |
| 18. | የቀረውን ማሰማርያችሁን በእግራችሁ የረገጣችሁት፥ በመልካሙ ማሰማርያ መሰማራታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? የቀረውንስ ውኃ በእግራችሁ ያደፈረሳችሁት፥ ጥሩውን ውኃ መጠጣታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? |
| 19. | በጎቼም በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ። |
| 20. | ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል። እነሆ፥ እኔ በወፈሩት በጎችና በከሱት በጎች መካከል እፈርዳለሁ። |
| 21. | እስክትበትኑአቸው ድረስ በእንቢያና በትከሻ ስለምትገፉአቸው የደከሙትንም ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው፥ |
| 22. | ስለዚህ መንጋዬን አድናለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ንጥቂያ አይሆኑም፤ በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ። |
| 23. | በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ እርሱም ያሰማራቸዋል፥ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው፤ ያሰማራቸዋል እረኛም ይሆናቸዋል። |
| 24. | እኔም እግዚአብሔር አምላክ እሆናቸዋለሁ ባሪያዬም ዳዊት በመካከላቸው አለቃ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ። |
| 25. | የሰላምን ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር እገባለሁ ክፉዎችንም አራዊት ከምድር አጠፋለሁ፤ ተዘልለውም በምድረ በዳ ይኖራሉ በዱርም ውስጥ ይተኛሉ። |
| 26. | እነርሱንና በኮረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች ለበረከት አደርጋቸዋለሁ፥ ዝናቡንም በጊዜው አወርዳለሁ፤ የበረከት ዝናብ ይሆናል። |
| 27. | የምድረ በዳም ዛፍ ፍሬውን ይሰጣል ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፥ በምድራቸውም ተዘልለው ይኖራሉ የቀንበራቸውንም ማነቆ በሰበርሁ ጊዜ ከሚገዙአቸውም እጅ ባዳንኋቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። |
| 28. | እንግዲህም ለአሕዛብ ንጥቂያ አይሆኑም የምድርም አራዊት አይበሉአቸውም፤ ተዘልለውም ይቀመጣሉ የሚያስፈራቸውም የለም። |
| 29. | የዝናን ተክል አቆምላቸዋለሁ እንግዲህም ከራብ የተነሣ በምድር አያልቁም፤ የአሕዛብንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አይሸከሙም። |
| 30. | እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንዳለሁ፥ እነርሱም የእስራኤል ቤት ሕዝቤ እንደ ሆኑ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
| 31. | እናንተም በጎቼ፥ የማሰማርያዬ በጎች፥ ሰዎች ናችሁ እኔም አምላካችሁ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
| ← Ezekiel (34/48) → |