← Ezekiel (33/48) → |
1. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
2. | የሰው ልጅ ሆይ፥ ለሕዝብህ ልጆች ተናገር እንዲህም በላቸው። ሰይፍን በምድር ላይ ባመጣሁ ጊዜ፥ የምድር ሕዝብ ከመካከላቸው ሰውን ወስደው ለራሳቸው ጕበኛ ቢያደርጉ፥ |
3. | እርሱም በምድር ላይ የመጣውን ሰይፍ ባየ ጊዜ መለከትን ቢነፋ ሕዝቡንም ቢያስጠነቅቅ፥ |
4. | የመለከቱን ድምፅ የሚሰማ ሰው ባይጠነቀቅ፥ ሰይፍ መጥቶ ቢወስደው፥ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል። |
5. | የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ስላልተጠነቀቀ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅስ ኖሮ ነፍሱን ባዳነ ነበር። |
6. | ጕበኛው ግን ሰይፍ ሲመጣ ቢያይ መለከቱንም ባይነፋ ሕዝቡንም ባያስጠነቅቅ ሰይፍም መጥቶ አንድ ሰው ከእርሱ ቢወስድ፥ እርሱ በኃጢአቱ ተወስዶአል ደሙን ግን ከጕበኛው እጅ እፈልጋለሁ። |
7. | አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ከአፌ ቃሌን ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። |
8. | ኃጢአተኛውን። ኃጢአተኛ ሆይ፥ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ ኃጢአተኛውን ከመንገዱ ታስጠነቅቅ ዘንድ ባትናገር ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። |
9. | ነገር ግን ከመንገዱ ይመለስ ዘንድ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል። |
10. | አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ቤት። እናንተ። በደላችንና ኃጢአታችን በላያችን አሉ እኛም ሰልስለንባቸዋል፤ እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችሁ ተናግራችኋል በላቸው። |
11. | እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው። |
12. | አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህን ልጆች እንዲህ በላቸው። በበደለበት ቀን የጻድቅ ጽድቁ አያድነውም፥ ኃጢአተኛም ከኃጢአቱ በተመለሰበት ቀን በኃጢአቱ አይሰናከልም፤ ጻድቁም ኃጢአት በሠራበት ቀን በጽድቁ በሕይወት አይኖርም። |
13. | እኔ ጻድቁን። በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ በጽድቁ ታምኖ ኃጢአት ቢሠራ በሠራው ኃጢአት ይሞታል እንጂ ጽድቁ አይታሰብለትም። |
14. | እኔም ኃጢአተኛውን። በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥ |
15. | ኃጢአተኛውም መያዣን ቢመልስ የነጠቀውንም ቢመልስ በሕይወትም ትእዛዝ ቢሄድ ኃጢአትም ባይሠራ፥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። |
16. | የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፤ ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአል፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል። |
17. | ነገር ግን የሕዝብህ ልጆች። የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ይላሉ፤ ነገር ግን የእነርሱ መንገድ የቀና አይደለም። |
18. | ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአትን ቢሠራ ይሞትባታል። |
19. | ኃጢአተኛውም ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ በሕይወት ይኖርበታል። |
20. | እናንተ ግን። የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ። |
21. | እንዲህም ሆነ፤ በተማረክን በአሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ። ከተማይቱ ተመታች አለኝ። |
22. | ያመለጠውም ሳይመጣ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ በነጋውም ወደ እኔ እስኪመጣ ድረስ አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተች ከዚያም በኋላ እኔ ዲዳ አልሆንሁም። |
23. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
24. | የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር ባሉ በባድማ ስፍራዎች የተቀመጡ። አብርሃም ብቻውን ሳለ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛም ብዙዎች ነን ምድሪቱም ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች ይላሉ። |
25. | ስለዚህ እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከደም ጋር ትበላላችሁ፥ ዓይናችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፥ ደምንም ታፈስሳላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? |
26. | ሰይፋችሁን ይዛችሁ ቆማችኋል፥ ርኩስ ነገርን ታደርጋላችሁ፥ የባልንጀሮቻችሁንም ሚስቶች ታስነውራላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? |
27. | እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና በባድማ ስፍራዎች ያሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ በምድረ በዳ ያለውን ለአራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ፥ በአምባዎችና በዋሾች ያሉ በቸነፈር ይሞታሉ። |
28. | ምድሪቱንም ባድማና ውድማ አደርጋታለሁ የኃይልዋም ትዕቢት ይቀራል፥ የእስራኤልም ተራሮች ባድማ ይሆናሉ፥ ማንም አያልፍባቸውም። |
29. | ስላደረጉትም ርኵሰት ሁሉ ምድሪቱን ባድማና ውድማ ባደርግሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። |
30. | አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህ ልጆች በቅጥር አጠገብና በቤት ደጆች ውስጥ ስለ አንተ ይናገራሉ፥ እርስ በርሳቸውም፥ አንዱ ከአንዱ ጋር። እንሂድና እግዚአብሔር ያለው ቃል ምን እንደ ሆነ እንስማ ብለው ይናገራሉ። |
31. | ሕዝብ እንደሚመጣ ወደ አንተ ይመጣሉ፥ እንደ ሕዝቤም በፊትህ ይቀመጣሉ፥ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም፤ በአፋቸው ብዙ ፍቅር ይገልጣሉ፥ ልባቸው ግን ስስታቸውን ትከተላለች። |
32. | እነሆ፥ አንተ መልካም ድምፅ እንዳለው እንደሚወደድ መዝሙር ማለፊያም አድርጎ በገና እንደሚጫወት ሰው ሆነህላቸዋል፤ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም። |
33. | እነሆ፥ ይህ ይመጣል፤ በመጣም ጊዜ እነርሱ ነቢይ በመካከላቸው እንደ ነበረ ያውቃሉ። |
← Ezekiel (33/48) → |