← Ezekiel (32/48) → |
1. | እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
2. | የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በለው። የአሕዛብን አንበሳ መስለህ ነበር፥ ነገር ግን እንደ ባሕር ዘንዶ ሆነሃል፤ በወንዞችህም ወጥተሃል፥ ወኃውንም በእግርህ አደፍርሰሃል፥ ወንዞችህንም አሳድፈሃል። |
3. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በብዙ አሕዛብ ጉባኤ መረቤን እዘረጋብሃለሁ፥ እነርሱም በመረቤ ያወጡሃል። |
4. | በምድርም ላይ እተውሃለሁ፥ በምድረ በዳም ፊት እጥልሃለሁ፥ የሰማይንም ወፎች ሁሉ አሳርፍብሃለሁ፥ የምድርንም አራዊት ሁሉ ከአንተ አጠግባቸዋለሁ። |
5. | ሥጋህን በተራሮች ላይ አደርጋለሁ ሸለቆቹንም በሬሳህ ክምር እሞላለሁ። |
6. | የምትዋኝባትንም ምድር እስከ ተራሮች ድረስ በደምህ አጠጣለሁ፥ መስኖችም ከአንተ ይሞላሉ። |
7. | ባጠፋሁህም ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶችንም አጨልማለሁ፤ ፀሐዩንም በደመና እሸፍናለሁ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም። |
8. | የሰማይን ብርሃኖች ሁሉ በላይህ አጨልማለሁ፥ በምድርህም ላይ ጨለማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
9. | በማታውቃቸውም አገሮች ባሉ በአሕዛብ ዘንድ ጥፋትህን ባመጣሁ ጊዜ የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ። |
10. | ብዙም አሕዛብን አስደንቅብሃለሁ ሰይፌንም በፊታቸው ባወዛወዝሁ ጊዜ ነገሥታቶቻቸው ስለ አንተ እጅግ አድርገው ይፈራሉ፤ በወደቅህበትም ቀን እያንዳንዱ ስለ ነፍሱ በየጊዜው ሁሉ ይንቀጠቀጣል። |
11. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣብሃል። |
12. | በኃያላን ሰይፍ የሕዝብህን ብዛት እጥላለሁ፤ ሁሉ የአሕዛብ ጨካኞች ናቸው፤ የግበጽንም ትዕቢት ያጠፋሉ ብዛትዋም ሁሉ ይጠፋል። |
13. | በብዙም ውኃ አጠገብ ያሉትን እንስሶች ሁሉ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ የሰው እግር አያደፈርሰውም የእንስሳም ኮቴ አይረግጠውም። |
14. | በዚያን ጊዜ ውኃቸውን አጠራለሁ፥ ወንዞቻቸውም እንደ ዘይት እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
15. | የግብጽንም ምድር ባድማና ውድማ ባደረግሁ ጊዜ፥ ሞላዋንም ያጣች ምድር ባደረግኋት ጊዜ፥ የሚኖሩባትንም ሁሉ በቀሠፍሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። |
16. | የሚያለቅሱበት ልቅሶ ይህ ነው፤ የአሕዛብ ቈነጃጅት ያለቅሱበታል፤ ስለ ግብጽና ስለ ብዛትዋ ሁሉ ያለቅሱበታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
17. | እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
18. | የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ብዛት ዋይ በል፥ እርስዋንና የብርቱዎችን አሕዛብ ሴቶች ልጆች ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ታችኛው ምድር ጣላቸው። |
19. | በውበት የምትበልጪው ማን ነው? ውረጂ ካልተገረዙትም ጋር ተኚ። |
20. | በሰይፍ በተገደሉት መካከል ይወድቃሉ፤ ለሰይፍ ተሰጥታለች፤ እርስዋንና ብዛትዋን ሁሉ ጐትቱ። |
21. | የኃያላን አለቆች በሲኦል ውስጥ ሆነው ከረዳቶቹ ጋር ይናገሩታል፤ በሰይፍም የተገደሉት ያልተገረዙ ወርደው ተኝተዋል። |
22. | አሦርና ጉባኤዋ ሁሉ በዚያ አሉ፤ መቃብራቸው በዙሪያቸው ነው፤ ሁሉም በሰይፍ ወድቀው ተገደሉ። |
23. | መቃብራቸው በጕድጓዱ በውስጠኛው ክፍል ነው፥ ጉባኤዋም በመቃብርዋ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል። |
24. | ኤላምም በዚያ አለች ብዛትዋም ሁሉ በመቃብርዋ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል ሳይገረዙም ወደ ታችኛው ምድር ወርደዋል፥ ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል። |
25. | በተገደሉት መካከል ከብዛትዋ ሁሉ ጋር መኝታን አድርገውላታል፤ መቃብርዋ በዙሪያዋ ነው ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፤ በሕያዋንም ምድር ያስፈሩ ነበር ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል፥ በተገደሉትም መካከል ተሰጥተዋል። |
26. | ሞሳሕና ቶቤል ብዛታቸውም ሁሉ በዚያ አሉ መቃብራቸውም በዙሪያቸው ነው፤ ሁሉም ሳይገረዙ በሰይፍ ተገድለዋል፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ነበርና። |
27. | በሕያዋንም ምድር ኃያላኑን ያስፈሩ ነበርና መሣሪያቸውን ይዘው ወደ ሲኦል ከወረዱ፥ ሰይፋቸውንም ከራሳቸው በታች ካደረጉ፥ ኃጢአታቸውም በአጥንታቸው ላይ ከሆነ ጋር ከወደቁ ካልተገረዙ ኃያላን ጋር ይተኛሉ። |
28. | አንተም ባልተገረዙት መካከል ትሰበራለህ፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ትተኛለህ። |
29. | ኤዶምያስና ነገሥታቶችዋ አለቆችዋም ሁሉ በዚያ አሉ፤ በሰይፍ ከተገደሉት ጋር በኃይላቸው ተኝተዋል፤ ካልተገረዙትና ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ይተኛሉ። |
30. | የሰሜን አለቆች ሁሉ ሲዶናውያንም ሁሉ ከተገደሉት ጋር ወርደው በዚያ አሉ፤ በኃይላቸውም ያስፈሩ በነበረው ፍርሃት አፍረዋል፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ሳይገረዙ ተኝተዋል፥ ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱት ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል። |
31. | በሰይፍ የተገደሉ ፈርዖንና ሠራዊቱ ሁሉ ያዩአቸዋል ፈርዖንም ስለ ብዛቱ ሁሉ ይጽናናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
32. | መፈራቱን በሕያዋን ምድር አድርጌአለሁ፥ ፈርዖንና ብዛቱም ሁሉ በሰይፍ በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ይተኛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
← Ezekiel (32/48) → |