Ezekiel (28/48)  

1. የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2. የሰው ልጅ ሆይ፥ የጢሮስን ገዥ እንዲህ በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ልብህ ኰርቶአል አንተም። እኔ አምላክ ነኝ፥ በእግዚአብሔር ወንበር በባሕር መካከል ተቀምጫለሁ ብለሃል፤ ነገር ግን ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ ብታደርግም አንተ ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም።
3. እነሆ፥ ከዳንኤል ይልቅ ጥበበኛ ነህ፥ ምሥጢርም ሁሉ ከአንተ የተሸሸገ አይደለም።
4. በጥበብህና በማስተዋልህ ብልጥግናን ለራስህ አግኝተሃል ወርቅና ብርም በግምጃ ቤትህ ውስጥ ሰብስበሃል።
5. በታላቅ ጥበብህና በንግድህ ብልጥግናህን አብዝተሃል በብልጥግናህም ልብህ ኰርቶአል።
6. ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ አድርገሃልና
7. ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሌላ አገር ሰዎችን፥ የአሕዛብን ጨካኞች፥ አመጣብሃለሁ፤ ሰይፋቸውንም በጥበብህ ውበት ላይ ይመዝዛሉ ክብርህንም ያረክሳሉ።
8. ወደ ጕድጓድ ያወርዱሃል፤ ተገድለው እንደ ሞቱ በባሕር ውስጥ ትሞታለህ።
9. በውኑ በገዳይህ ፊት። እኔ አምላክ ነኝ ትላለህን? ነገር ግን በገዳይህ እጅ ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም።
10. በእንግዶች እጅ ያልተገረዙትን ሰዎች ሞት ትሞታለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
11. የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
12. የሰው ልጅ ሆይ፥ በጢሮስ ንጉሥ ላይ ሙሾ አሞሽተህ እንዲህ በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጥበብን የተሞላህ ውበትህም የተፈጸመ መደምደሚያ አንተ ነህ።
13. በእግዚአብሔር ገነት በዔድን ነበርህ፤ የከበረ ዕንቍስ ሁሉ፥ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ አልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ፥ ሰንፔር፥ በሉር፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ወርቅ፥ ልብስህ ነበረ፤ የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ፤ በተፈጠርህበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር።
14. አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ፤ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ።
15. ከተፈጠርህበት ቀን ጀምረህ በደል እስኪገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ።
16. በንግድህ ብዛት ግፍ በውስጥህ ተሞላ ኃጢአትንም ሠራህ፤ ስለዚህ እንደ ርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ፤ የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ፥ ከእሳት ድንጋዮች መካከል አጠፋሁህ።
17. በውበትህ ምክንያት ልብህ ኰርቶአል፤ ከክብርህ የተነሣ ጥበብህን አረከስህ፤ በምድር ላይ ጣልሁህ ያዩህም ዘንድ በነገሥታት ፊት ሰጠሁህ።
18. በበደልህ ብዛት በንግድህም ኃጢአት መቅደስህን አረከስህ፤ ስለዚህ እሳትን ከውስጥህ አውጥቻለሁ እርስዋም በልታሃለች፥ በሚያዩህም ሁሉ ፊት በምድር ላይ አመድ አድርጌሃለሁ።
19. በአሕዛብም ውስጥ የሚያውቁህ ሁሉ ይደነቁብሃል፤ አንተም ለድንጋጤ ሆነሃል፥ እስከ ዘላለምም አትገኝም።
20. የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
21. የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሲዶና አቅንተህ ትንቢት ተናገርባት፥ እንዲህም በል።
22. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሲዶና ሆይ፥ እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ በውስጥሽም እከብራለሁ፤ ፍርድንም ባደረግሁባት ጊዜ በተቀደስሁባትም ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
23. ቸነፈርንም በእርስዋ ላይ፥ ደምንም በጎዳናዋ እሰድዳለሁ፤ ከዙሪያዋ በላይዋ ባለ ሰይፍ የተወጉ በመካከልዋ ይወድቃሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
24. ከእንግዲህም ወዲያ ለእስራኤል ቤት የሚወጋ እሾህ፥ በዙሪያቸውም ካሉ ካናቋቸው ሁሉ የሚያቈስል ኵርንችት አይሆንም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
25. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤልን ቤት ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ በሰበሰብሁ ጊዜ፥ በአሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድራቸው ይቀመጣሉ።
26. ተዘልለውም ይቀመጡባታል፤ ቤቶችንም ይሠራሉ ወይኑንም ይተክላሉ በዙሪያቸውም ባሉ በሚንቋቸው ሁሉ ላይ ፍርድን ባደረግሁ ጊዜ ተዘልለው ይቀመጣሉ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

  Ezekiel (28/48)