← Ezekiel (27/48) → |
1. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
2. | አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ጢሮስ ሙሾ አድርግ፥ |
3. | በባሕር መግቢያ የምትኖር በብዙም ደሴቶች ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ጋር ንግድን የምታደርግ ጢሮስንም እንዲህ በላት። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጢሮስ ሆይ፥ አንቺ። በውበት ፍጹም ነኝ ብለሻል። |
4. | ዳርቻሽ በባሕር ውስጥ ነው፤ ሠሪዎችሽ ውበትሽን ፈጽመዋል። |
5. | ሳንቃዎችሽን ሁሉ ከሳኔር ጥድ ሠርተዋል፥ ደቀልንም ይሠሩልሽ ዘንድ ከሊባኖስ ዝግባ ወስደዋል። |
6. | ከባሳን ኮምቦል መቅዘፊያሽን ሠርተዋል፥ በዝሆን ጥርስ ከታሻበ ከኪቲም ደሴቶች ዛፍ መቀመጫዎችሽን ሠርተዋል። |
7. | ዓላማ እንዲሆንልሽ ሸራሽ ከግብጽ በፍታና ከወርቅ ዘቦ ተሠርቶአል፥ መደረቢያሽም ከኤሊሳ ደሴቶች ሰማያዊና ቀይ ሐር ተሠርቶአል። |
8. | የሲዶናና የአራድ ሰዎች ቀዛፎችሽ ነበሩ፤ ጢሮስ ሆይ፥ ጥበበኞችሽ በአንቺ ዘንድ ነበሩ የመርከቦችሽም መሪዎች ነበሩ። |
9. | በአንቺ ውስጥ የነበሩ የጌባል ሽማግሌዎችና ጥበበኞችዋ ስብራትሽን ይጠግኑ ነበር፤ ከአንቺም ጋር ይነግዱ ዘንድ የባሕር መርከቦች ሁሉና መርከበኞቻቸው በመካከልሽ ነበሩ። |
10. | ፋርስና ሉድ ፉጥም በሠራዊትሽ ሰልፈኞችሽ ነበሩ፤ ጋሻና ራስ ቍርም በአንቺ ውስጥ ያንጠለጥሉ ነበር፤ እነርሱም ውበትሽን ሰጡ። |
11. | የአራድ ሰዎችና ሠራዊቶችሽ በቅጥሮችሽ ላይ በዙሪያ ነበሩ፥ ገማዳውያንም በግንቦችሽ ውስጥ ነበሩ፤ ጋሻቸውንም በዙሪያ በቅጥርሽ ላይ አንጠለጠሉ፥ ውበትሽንም ፈጽመዋል። |
12. | ከብልጥግናሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ ተርሴስ ነጋዴሽ ነበረች፤ በብርና በብረት በቈርቈሮና በእርሳስ ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። |
13. | ያዋንና ቶቤል ሞሳሕም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ የሰዎችን ነፍሳትና የናሱን ዕቃ ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። |
14. | ከቴርጋማ ቤትም የነበሩት ሰዎች በፈረሶችና በፈረሰኞች በበቅሎዎችም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። |
15. | የድዳን ሰዎች ነጋዴዎችሽ ነበሩ። ብዙ ደሴቶች የእጅሽ ገበያዎች ነበሩ፤ ይለውጡ ዘንድ የዝሆን ጥርስና ዞጲ አመጡልሽ። |
16. | ከሥራሽ ብዛት የተነሣ ሶርያ ነጋዴሽ ነበረች በበሉርና በቀይ ሐር በወርቀ ዘቦም በጥሩ በፍታም በዛጐልም በቀይ ዕንቍም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። |
17. | ይሁዳና የእስራኤል ምድር ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ የሚኒትን ስንዴ ጣፋጭም እንጐቻ፥ ማር ዘይትም በለሳንም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። |
18. | ከሥራሽ ብዛትና ከብልጥግናሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ ደማስቆ ነጋዴሽ ነበረች፤ በኬልቦን የወይን ጠጅ በነጭም በግ ጠጕር ይነግዱ ነበር። |
19. | ዌንዳንና ያዋን ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር፤ ከኦሴል የተሠራ ብረትና ብርጕድ ቀረፋም ሸቀጥሽ ነበረ። |
20. | ድዳን በከብት ላይ ለመቀመጥ በመረሻት ነጋዴሽ ነበረች። |
21. | ዓረብና የቄዳር አለቆች ሁሉ የእጅሽ ነጋዴዎች ነበሩ፤ በጠቦቶችና በአውራ በጎች በፍየሎችም በእነዚህ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር። |
22. | የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች እነዚህ ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ በጥሩ ሽቶና በክብር ድንጋይ ሁሉ በወርቅም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። |
23. | ካራንና ካኔ ዔድንም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ አሦርና ኪልማድ ነጋዴዎችሽ ነበሩ። |
24. | እነዚህ ባማረ ልብስ በሰማያዊ ካባ በወርቀ ዘቦም፥ በዝግባ በተሠራች በገመድም በታሰረች በግምጃም በተሞላች ሳጥን በገበያሽ ይነግዱ ነበር። |
25. | የተርሴስ መርከቦች ሸቀጥሽን የሚሸከሙ ነበሩ፤ አንቺም ተሞልተሽ ነበር በባሕርም ውስጥ እጅግ ከበርሽ። |
26. | ቀዛፊዎችሽ ወደ ትልቁ ወኃ አመጡሽ፤ የምሥራቅ ነፋስ በባሕር ውስጥ ሰበረሽ። |
27. | ብልጥግናሽና ሸቀጥሽ ንግድሽም መርከበኞችሽም መርከብ መሪዎችሽም ሰባራሽንም የሚጠግኑ ነጋዴዎችሽም በአንቺም ዘንድ ያሉ ሰልፈኞችሽ ሁሉ በውስጥሽ ካሉት ጉባኤ ሁሉ ጋር በወደቅሽበት ቀን በባሕር ውስጥ ይወድቃሉ። |
28. | ከመርከብ መሪዎች ጩኸት ድምፅ የተነሣ በዙሪያሽ ያሉ ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ። |
29. | ቀዛፊዎችም ሁሉ መርከበኞችም መርከብ መሪዎችም ሁሉ ከመርከቦቻቸው ይወርዳሉ በመሬትም ላይ ይቆማሉ፤ |
30. | ድምፃቸውንም በአንቺ ላይ ያሰማሉ፥ ምርር ብለውም ይጮኻሉ፥ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ይነሰንሳሉ፥ በአመድም ውስጥ ይንከባለላሉ፤ |
31. | ስለ አንቺም የራሳቸውን ጠጕር ይላጫሉ ማቅም ያሸርጣሉ በነፍስ ምሬትም ስለ አንቺ መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ። |
32. | በትካዜያቸውም ልቅሶ ያነሡልሻል፥ ስለ አንቺም ሙሾ ያሞሻሉ እንዲህም ይላሉ። በባሕር መካከል ጠፍቶ እንደ ቀረ እንደ ጢሮስ ያለ ማን ነው? |
33. | ሸቀጥሽ ከባሕር በወጣ ጊዜ ብዙ አሕዛብን አጥግበሻል፤ በብልጥግናሽና በንግድሽ ብዛት የምድርን ነገሥታት ባለ ጠጎች አድርገሻል። |
34. | አሁን ግን በጥልቅ ውኃ ውስጥ በባህር ተሰብረሻል ንግድሽና ጉባኤሽ ሁሉ በመካከልሽ ወድቀዋል። |
35. | በደሴቶሽ የሚኖሩ ሁሉ ተደንቀውብሻል፥ ነገሥታቶቻቸውም እጅግ ፈርተዋል ፊታቸውም ተለውጦአል። |
36. | የአሕዛብ ነጋዴዎች አፍዋጩብሽ፤ አንቺ ለድንጋጤ ሆነሻል፥ እስከ ዘላለምም አትገኚም። |
← Ezekiel (27/48) → |