| ← Ezekiel (26/48) → |
| 1. | እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ አንደኛው ዓመት ከወሩ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
| 2. | የሰው ልጅ ሆይ፥ ጢሮስ በኢየሩሳሌም ላይ። እሰይ፥ የአሕዛብ በር የነበረች ተሰብራለች ወደ እኔም ተመልሳለች፤ እርስዋ ፈርሳለችና እኔ እሞላለሁ ብላለችና |
| 3. | ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጢሮስ ሆይ፥ እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ባሕርም ሞገድዋን እንደምታወጣ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን አወጣብሻለሁ። |
| 4. | የጢሮስንም ቅጥሮች ያጠፋሉ ግንቦችዋንም ያፈርሳሉ፤ ትቢያዋንም ከእርስዋ እፍቃለሁ፥ የተራቈተ ድንጋይም አደርጋታለሁ። |
| 5. | በባሕር ውስጥ የመረብ ማስጫ ትሆናለች፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለአሕዛብም ብዝበዛ ትሆናለች። |
| 6. | በሜዳ ያሉትም ሴቶች ልጆችዋ በሰይፍ ይገደላሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። |
| 7. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ከሰሜን የነገሥታት ንጉሥ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ከፈረሶችና ከሰረገሎች ከፈረሰኞችም ከጉባኤና ከብዙ ሕዝብ ጋር በጢሮስ ላይ አመጣለሁ። |
| 8. | በሜዳ ያሉትን ሴቶች ልጆችሽን በሰይፍ ይገድላቸዋል፥ አምባም ይሠራብሻል አፈርንም ይደለድልብሻል ጋሻም ያነሣብሻል። |
| 9. | ማፍረሻውን በቅጥርሽ ላይ ያደርጋል፥ ግንቦችሽንም በምሳር ያፈርሳል። |
| 10. | ከፈረሶቹም ብዛት የተነሣ ትቢያቸው ይከድንሻል፤ ሰዎችም በተናደች ቅጥር ወደ ከተማ እንደሚገቡ እርሱ በበሮችሽ ሲገባ፥ ከፈረሰኞችና ከመንኰራኵሮች ከሰረገሎችም ድምፅ የተነሣ ቅጥርሽ ትናወጣለች። |
| 11. | በፈረሶቹ ኮቴ ጎዳናዎችሽን ሁሉ ይረመርማል፥ ሕዝብሽንም በሰይፍ ይገድላል፥ የብርታትሽም ሐውልት ወደ ምድር ይወድቃል። |
| 12. | ብልጥግናሽንም ይማርካሉ፥ ሸቀጥሽንም ይበዘብዛሉ፤ ቅጥርሽንም ያፈርሳሉ፥ ተድላ የምታደርጊባቸውን ቤቶችሽን ያጠፋሉ፤ ድንጋይሽንና እንጨትሽን መሬትሽንም በባሕር ውስጥ ይጥላሉ። |
| 13. | የዘፋኞችሽንም ብዛት ዝም አሰኛለሁ፤ የመሰንቆሽም ድምፅ ከዚያ ወዲያ አይሰማም። |
| 14. | የተራቈተ ድንጋይ አደርግሻለሁ የመረብም ማስጫ ትሆኛለሽ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አትሠሪም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። |
| 15. | ጌታ እግዚአብሔር ጢሮስን እንዲህ ይላታል። የተወጉት ባንቋረሩ ጊዜ፥ በውስጥሽ እልቂት በሆነ ጊዜ፥ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሣ ደሴቶች ይነዋወጡ የለምን? |
| 16. | የባሕርም አለቆች ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ መጐናጸፊያቸውን ያወጣሉ ወርቀ ዘቦ ልብሳቸውንም ያወልቃሉ፤ መንቀጥቀጥን ለብሰው በመሬት ላይ ይቀመጣሉ፥ ሁልጊዜም ይንቀጠቀጣሉ በአንቺም ይደነቃሉ። |
| 17. | በአንቺም ላይ ሙሾ ያሞሻሉ፥ እንዲህም ይሉሻል። በባሕር የተቀመጥሽ በባሕርም ውስጥ የጸናሽ፥ ከሚቀመጡብሽም ጋር በዙሪያሽ የሚኖሩትን ሁሉ ያስፈራሽ፥ የከበርሽ ከተማ ሆይ፥ እንዴት ጠፋሽ! |
| 18. | አሁን በውድቀትሽ ቀን ደሴቶች ይንቀጠቀጣሉ፥ በባሕርም ውስጥ ያለ ደሴቶች ከመጥፋትሽ የተነሣ ይደነግጣሉ። |
| 19. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ሰው እንደሌለባቸው ከተሞች ባድማ ከተማ ባደረግሁሽ ጊዜ፥ ቀላዩንም ባወጣሁብሽ ጊዜ ብዙ ውኆችም በከደኑሽ ጊዜ፥ |
| 20. | የቀድሞ ሕዝብ ወዳሉበት ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋር አወርድሻለሁ፤ የሚኖርብሽም እንዳይገኝ ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ቀድሞ በፈረሰችው ስፍራ፥ በታችኛይቱ ምድር አኖርሻለሁ፤ ጌጥሽንም በሕያዋን ምድር አላኖርም። |
| 21. | ለድንጋጤ አደርግሻለሁ እንግዲህም አትኖሪም፤ ትፈለጊአለሽ ለዘላለምም አትገኚም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
| ← Ezekiel (26/48) → |