| ← Ezekiel (25/48) → | 
| 1. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። | 
| 2. | የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ አሞን ልጆች አቅንተህ ትንቢት ተናገርባቸው። | 
| 3. | ለአሞንም ልጆች እንዲህ በል። የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። መቅደሴ በረከሰ ጊዜ የእስራኤልም ምድር ባድማ በሆነች ጊዜ የይሁዳም ቤት በተማረኩ ጊዜ ስለ እነርሱ እሰይ ብለሃልና | 
| 4. | ስለዚህ፥ እነሆ፥ ርስት አድርጌ ለምሥራቅ ልጆች አሳልፌ አሰጥሃለሁ፥ እነርሱም በአንተ ውስጥ ይሰፍራሉ፥ ማደሪያዎቻቸውንም በአንተ ዘንድ ይሠራሉ፤ ፍሬህን ይበላሉ ወተትህንም ይጠጣሉ፤ | 
| 5. | የአሞንን ከተማ ለግመሎች ማሰማርያ፥ የአሞንንም ልጆች ለመንጋ መመሰጊያ አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። | 
| 6. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በእጅህ አጨብጭበሃልና፥ በእግርህም አሸብሽበሃልና፥ በእስራኤልም ምድር ላይ በነፍስህ ንቀት ሁሉ ደስ ብሎሃልና | 
| 7. | ስለዚህ፥ እነሆ፥ እጄን ዘርግቼብሃለህ፥ ለአሕዛብም አስበዘብዝሃለሁ፥ ከአሕዛብም ለይቼ እቈርጥሃለሁ፥ ከአገሮችም አጠፋሃለሁ እፈጅህማለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ። | 
| 8. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሞዓብና ሴይር። እነሆ፥ የይሁዳ ቤት እንደ አሕዛብ ሁሉ ነው ብለዋልና | 
| 9. | ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሞዓብን ጫንቃ ከከተሞቹ፥ በዳርቻው ካሉት የምድሩ ትምክሕት ከሆኑት ከተሞቹ፥ ከቤትየሺሞት፥ ከበኣልሜዎን፥ | 
| 10. | ከቂርያታይም፥ ከአሞን ልጆች ጋር ለምሥራቅ ልጆች እከፍታለሁ። የአሞን ልጆች በአሕዛብ መካከል ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታሰቡ ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ። | 
| 11. | በሞዓብም ላይ ፍርድን አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። | 
| 12. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ኤዶምያስ በይሁዳ ቤት ላይ በቀል አድርጎአልና፥ ቂም ይዞአልና፥ ብድራትንም አስከፍሎአልና | 
| 13. | ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እጄን በኤዶምያስ ላይ እዘረጋለሁ ከእርስዋም ዘንድ ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፥ ከቴማንም ጀምሮ ባድማ አደርጋታለሁ፥ እስከ ድዳንም ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ። | 
| 14. | በሕዝቤ በእስራኤል እጅ ኤዶምያስን እበቀላለሁ፤ እንደ ቍጣዬና እንደ መዓቴም መጠን በኤዶምያስ ያደርጋሉ፤ በቀሌንም ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። | 
| 15. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ፍልስጥኤማውያን በቀልን አድርገዋልና፥ በዘወትርም ጠላትነት ያጠፉ ዘንድ በነፍሳቸው ንቀት ተበቅለዋልና | 
| 16. | ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እጄን በፍልስጥኤማውያን ላይ እዘረጋለሁ፥ ከሊታውያንንም እቈርጣለሁ፥ የባሕሩንም ዳር ቅሬታ አጠፋለሁ። | 
| 17. | በመዓት መቅሠፍትም ታላቅ በቀል አደርግባቸዋለሁ፤ በቀሌንም በላያቸው ባደረግሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። | 
| ← Ezekiel (25/48) → |