← Ezekiel (23/48) → |
1. | የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
2. | የሰው ልጅ ሆይ፥ የአንዲት እናት ልጆች የሆኑ ሁለት ሴቶች ነበሩ። |
3. | በግብጽም አመነዘሩ፥ በኰረዳነታቸው አመነዘሩ፤ በዚያ ጡቶቻቸው ምዋሸሹ በዚያም የድንግልናቸውን ጡቶች ዳበሱ። |
4. | ስማቸውም የታላቂቱ ኦሖላ የእኅትዋም ኦሖሊባ ነበረ፥ ለእኔም ሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለዱ። ስማቸውም ኦሖላ ሰማርያ ናት፤ ኦሖሊባ ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት። |
5. | ኦሖላም ገለሞተችብኝ፥ ውሽሞችዋንም ጎረቤቶችዋን አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው። |
6. | እነርሱም ሰማያዊ ሐር የለበሱ አለቆችና ሹማምቶች፥ መልከ መልካሞች ጐበዛዝት፥ በፈረስ ላይ የሚቀመጡ ፈረሰኞች ነበሩ። |
7. | ግልሙትናዋንም ከተመረጡ ከአሦር ሰዎች ሁሉ ጋር አደረገች፥ በፍቅር በተከተለቻቸውም ጣዖቶቻቸው ሁሉ ረከሰች። |
8. | በግብጽም የነበረውን ግልሙትናዋን አልተወችም፤ በዚያ በኰረዳነትዋ ጊዜ ከእርስዋ ጋር ተኝተው ነበር፥ የድንግልናዋንም ጡቶች ዳብሰው ነበር፥ ግልሙትናቸውንም አፍስሰውባት ነበር። |
9. | ስለዚህ በፍቅር በተከተለቻቸው በውሽሞችዋ በአሦራውያን እጅ አሳልፌ ሰጠኋት። |
10. | እነርሱም ኅፍረተ ሥጋዋን ገለጡ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋንም ማርከው ወሰዱ፥ እርስዋንም በሰይፍ ገደሉ፤ ፍርድንም ስላደረጉባት በሴቶች መካከል መተረቻ ሆነች። |
11. | እኅትዋም ኦሖሊባ ይህን አየች፤ ሆኖም ከእርስዋ ይልቅ በፍቅር በመከተልዋ ረከሰች፥ ግልሙትናዋም ከእኅትዋ ግልሙትና ይልቅ በዛ። |
12. | አለቆችንና ሹማምቶችን ጎረቤቶችዋን ጌጠኛ ልብስ የለበሱትን በፈረሶች ላይ የሚቀመጡትን ፈረሰኞች፥ ሁሉም መልከ መልካሞችን ጐበዛዝት አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው። |
13. | የረከሰችም እንደ ሆነች አየሁ፥ ሁለቱም አንድ መንገድ ሄደዋል። |
14. | ግልሙትናዋንም አበዛች፤ በቀይ ቀለምም የተሳለችውን የከለዳውያንን ስዕል፥ በናስ ላይ የተሳሉትን ሰዎች አየች። |
15. | በወገባቸው ዝናር የታጠቁ ራሳቸውንም በቀለማዊ መጠምጠሚያ የጠመጠሙ ነበሩ፤ ሁሉም ከተወለዱባት አገር የሆኑትን የከለዳውያንን ልጆች መስለው መሳፍንትን ይመስሉ ነበር። |
16. | ባየቻቸውም ጊዜ በፍቅር ተከተለቻቸው፥ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ እነርሱ መልእክተኞችን ላከች። |
17. | የባቢሎንም ሰዎች ወደ እርስዋ ፍቅር ወዳለበት መኝታ መጡ በግልሙትናቸውም አረከሱአት፤ እርስዋም ከእነርሱ ጋር ረከሰች ነፍስዋም ከእነርሱ ተለየች። |
18. | ግልሙትናዋንም ገለጠች ኅፍረተ ሥጋዋንም አሳየች፤ ነፍሴም ከእኅትዋ እንደ ተለየች እንዲሁ ነፍሴ ከእርስዋ ተለየች። |
19. | ነገር ግን በግብጽ ምድር የገለሞተችበትን የኰረዳነትዋን ዘመን አስባ ግልሙትናዋን አበዛች። |
20. | ሥጋቸውም እንደ አህዮች ሥጋ ዘራቸውም እንደ ፈረሶች ዘር የሆነውን እነዚያን ምልምሎች በፍቅር ተከተለቻቸው። |
21. | ስለ ኰረዳነትሽ ምክንያት ግብጻውያን ጡቶችሽን በዳበሱ ጊዜ የኰረዳነትሽን ሴሰኝነት አሰብሽ። |
22. | ስለዚህ፥ ኦሖሊባ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፍስሽ ከእነርሱ የተለየች ውሽሞችሽን አስነሣብሻለሁ፥ በዙሪያሽም በአንቺ ላይ አመጣቸዋለሁ። |
23. | እነርሱም የባቢሎን ሰዎች ከለዳውያንም ሁሉ፥ ፋቁድ፥ ሱሔ፥ ቆዓ፥ ከእነርሱም ጋር አሦራውያን ሁሉ፥ መልከ መልካሞች ጐበዛዝት፥ አለቆችና ሹማምቶች ሁሉ፥ መሳፍንቶችና አማካሪዎች ሁሉ፥ በፈረስ ላይ የተቀመጡ ናቸው። |
24. | በመሣሪያና በሰረገላ በመንኰራኵርም በአሕዛብም ጉባኤ ይመጡብሻል፤ ጋሻና አላባሽ ጋሻ ራስ ቍርም ይዘው በዙሪያሽ ይዘጋጁብሻል፤ ፍርድንም እሰጣቸዋለሁ፥ እንደ ፍርዳቸውም ይፈርዱብሻል። |
25. | ቅንዓቴንም በአንቺ ላይ አደርጋለሁ በመዓትም ያደርጉብሻል፤ አፍንጫሽንና ጆሮሽንም ከአንቺ ይቈርጣሉ፥ ከአንቺም የቀረ በሰይፍ ይወድቃል፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽንም ማርከው ይወስዳሉ፥ ከአንቺም የቀረውን እሳት ትበላቸዋለች። |
26. | ልብስሽንም ይገፍፉሻል የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ። |
27. | ሴሰኝነትሽንም፥ ከግብጽ ምድር ያወጣሽውን ግልሙትናሽንም ከአንቺ አስቀራለሁ፤ ዓይንሽንም ወደ እነርሱ አታነሺም ግብጽንም ከዚያ ወዲያ አታስቢም። |
28. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ በጠላሻቸው እጅ፥ ነፍስሽ በተለየቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ |
29. | እነርሱም በጥል ያደርጉብሻል፥ የደከምሽበትንም ሁሉ ይወስዳሉ፥ ዕራቁትሽንና ዕርቃንሽን አድርገውም ይተዉሻል፤ የግልሙትናሽም ነውር፥ ሴሰኝነትሽና ግልሙትናሽም ሁሉ ይገለጣል። |
30. | ከአሕዛብ ጋር ስላመነዘርሽ በጣዖቶቻቸውም ስለ ረከስሽ ይህን ያደረጉብሻል። |
31. | በእኅትሽ መንገድ ሄደሻል፤ ስለዚህ ጽዋዋን በእጅሽ እሰጥሻለሁ። |
32. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የጠለቀውንና የሰፋውን ብዙም የሚይዘውን የእኅትሽን ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ መሳቂያና መሳለቂያም ትሆኛለሽ። |
33. | በእኅትሽ በሰማርያ ጽዋ፥ በድንጋጤና በጥፋት ጽዋ፥ በስካርና በውርደት ትሞልያለሽ። |
34. | ትጠጪዋለሽ ትጨልጪውማለሽ ገሉንም ታኝኪዋለሽ ጡትሽንም ትሸነትሪዋለሽ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። |
35. | ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዘንግተሽኛልና፥ ወደ ኋላሽም ጥለሽኛልና አንቺ ደግሞ ሴሰኝነትሽንና ግልሙትናሽን ተሸከሚ። |
36. | እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በኦሖላና በኦሖሊባ ትፈርዳለህን? ኃጢአታቸውንም ታስታውቃቸዋለህ? |
37. | አመንዝረዋልና፥ ደምም በእጃቸው አለና፥ ከጣዖቶቻቸውም ጋር አመንዝረዋልና፥ ለእኔም የወለዱአቸውን ልጆቻቸውን መብል እንዲሆኑላቸው በእሳት አሳልፈዋቸዋልና። |
38. | ይህን ደግሞ አድርገውብኛል፤ በዚያ ቀን መቅደሴን አርክሰዋል ሰንበታቴንም ሽረዋል። |
39. | ልጆቻቸውንም ለጣዖቶቻቸው በሠዉ ጊዜ፥ በዚያው ቀን ያረክሱት ዘንድ ወደ መቅደሴ ገቡ፤ እነሆም፥ በቤቴ ውስጥ እንደዚህ አደረጉ። |
40. | ደግሞ መልእክተኛ ወደ ተላከባቸው ከሩቅም ወደሚመጡ ሰዎች ልካችኋል፤ እነሆም መጡ፥ አንቺም ታጠብሽላቸው ዓይኖችሽንም ተኳልሽ ጌጥም አጌጥሽ፤ |
41. | በክብር አልጋ ላይ ተቀመጥሽ፥ በፊት ለፊትዋም ማዕድ ተዘጋጅታ ነበር፥ ዕጣኔንና ዘይቴንም አኖርሽባት። |
42. | የደስተኞችም ድምፅ በእርስዋ ዘንድ ነበረ፤ ከብዙም ሰዎች ጉባኤ ጋር ሰካራሞቹ ከምድረ በዳ መጡ፤ በእጃቸው አንበር በራሳቸውም የተዋበ አክሊል አደረጉ። |
43. | እኔም በምንዝር ላረጀችው። አሁን ከእርስዋ ጋር ያመነዝራሉ እርስዋም ከእነርሱ ጋር ታመነዝራለች አልሁ። |
44. | ወደ ጋለሞታም እንደሚገቡ ወደ እርስዋ ገቡ፤ እንዲሁ ይሰስኑ ዘንድ ወደ ኦሖላና ወደ ኦሖሊባ ገቡ። |
45. | ሴቶቹ አመንዝሮች ናቸውና፥ በእጃቸውም ደም አለና ጻጽቃን ሰዎች በአመንዝሮቹና በደም አፍሳሾቹ ሴቶች ላይ በሚፈረደው ፍርድ ይፈርዱባቸዋል። |
46. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጉባኤን አመጣባቸዋለሁ፥ ለመበተንና ለመበዝበዝም አሳልፌ አሰጣቸዋለሁ። |
47. | ጉባኤውም በድንጋይ ይወግሩአቸዋል በሰይፋቸውም ይቈርጡአቸዋል፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም ይገድላሉ፥ ቤቶቻቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ። |
48. | ሴቶችም ሁሉ እንደ ሴሰኝነታችሁ እንዳይሠሩ ይማሩ ዘንድ ሴሰኝነትን ከምድር ላይ አጠፋለሁ። |
49. | ሴሰኝነታችሁንም በላያችሁ ላይ ይመልሳሉ፥ እናንተም የጣዖቶቻችሁን ኃጢአት ትሸከማላችሁ፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። |
← Ezekiel (23/48) → |