| ← Ezekiel (22/48) → |
| 1. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
| 2. | አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ትፈርዳለህን? ደም በምታፈስስ ከተማ ላይ ትፈርዳለህን? ርኵሰትዋን ሁሉ አስታውቃት። |
| 3. | እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጊዜሽ እንዲደርስ በመካከልሽ ደምን የምታፈስሺ እንድትረክሺም በራስሽ ላይ ጣዖታትን የምታደርጊ ከተማ ሆይ! |
| 4. | ባፈሰስሽው ደም በድለሻል ባደረግሽውም ጣዖታት ረክሰሻል፤ ቀንሽን አቀረብሽ ዘመንሽንም አሳጠርሽ፤ ስለዚህ ለአሕዛብ መሰደቢያ ለአገሮችም ሁሉ መሳለቂያ አደረግሁሽ። |
| 5. | አንቺ ስምሽ የረከሰ ሽብርም የሞላብሽ ሆይ፥ ወደ አንቺ የቀረቡና ከአንቺ የራቁ ይሳለቁብሻል። |
| 6. | እነሆ፥ የእስራኤል አለቆች እያንዳንዱ እንደ ችሎቱ ደም ያፈስሱ ዘንድ በአንቺ ውስጥ ነበሩ። |
| 7. | በአንቺ ውስጥ አባትንና እናትን አቃለሉ፤ በመካከልሽ በመጻተኛው ላይ በደልን አደረጉ፤ በአንቺ ውስጥ ድሀ አደጉንና መበለቲቱን አስጨነቁ። |
| 8. | ቅድሳቴንም ናቅሽ ሰንበታቴንም አረከስሽ። |
| 9. | ደምን ያፈስሱ ዘንድ ቀማኞች ሰዎች በአንቺ ውስጥ ነበሩ፤ በአንቺ ውስጥ በተራሮች ላይ በሉ፤ በመካከልሽ ሴሰኝነትን አደረጉ። |
| 10. | በአንቺ ውስጥ የአባቶቻቸውን ኀፍረተ ሥጋ ገለጡ፤ በአንቺም ውስጥ አደፍ ያለባትን አዋረዱ። |
| 11. | ሰውም በባልንጀራው ሚስት ርኵሰትን አደረገ፥ አባትም የልጁን ሚስት አረከሰ፥ በአንቺም ዘንድ ወንድም የአባቱን ልጅ እኅቱን አሳፈረ። |
| 12. | በአንቺ ውስጥ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ጉቦን ተቀበሉ፤ አንቺም አራጣና ትርፍ ወስደሻል፥ ከባልንጀሮችሽም በቅሚያ የስስትን ትርፍ አገኘሽ፥ እኔንም ረሳሽኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
| 13. | ስለዚህ፥ እነሆ፥ አንቺ ባደረግሽው ስስት በመካከልሽም በነበረው ደም ላይ እጄን አጨበጨብሁ። |
| 14. | በውኑ እኔ በማደርግብሽ ወራት ልብሽ ይታገሣልን? ወይስ እጅሽ ትጸናለችን? እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ አደርገውማለሁ። |
| 15. | ወደ አሕዛብም እበትንሻለሁ ወደ አገሮችም እዘራሻለሁ፥ ርኵሰትሽንም ከአንቺ ዘንድ አጠፋለሁ። |
| 16. | በአሕዛብም ፊት አንቺ ትረክሻለሽ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂአለሽ። |
| 17. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
| 18. | የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት ለእኔ እንደ አተላ ሆኑብኝ፤ እነርሱ ሁሉ በከውር ውስጥ መዳብና ቈርቈሮ ብረትና እርሳስ ናቸው፤ የብር አተላ ናቸው። |
| 19. | ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሁላችሁ አተላ ሆናችኋልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ በኢየሩሳሌም ውስጥ እሰበስባችኋለሁ። |
| 20. | እንዲያቀልጡት እሳት ያናፉበት ዘንድ ብርንና መዳብን ብረትንና እርሳስን ቈርቈሮንም በከውር እንደሚሰበስቡ፥ እንዲሁ በቍጣዬና በመዓቴ እሰበስባችኋለሁ፥ በዚያም ውስጥ እጨምራችኋለሁ አቀልጣችሁማለሁ። |
| 21. | አሰበስባችሁማለሁ የመዓቴንም እሳት አናፋባችኋለሁ በውስጡም ትቀልጣላችሁ። |
| 22. | ብርም በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ በውስጡዋ ትቀልጣላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር መዓቴን እንዳፈሰስሁባችሁ ታውቃላችሁ። |
| 23. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
| 24. | የሰው ልጅ ሆይ። አንቺ ያልነጻሽ በቍጣም ቀን ያልዘነበብሽ ምድር ነሽ በላት። |
| 25. | በውስጥዋ ያሉ ነቢያት እንደሚጮኽና እንደሚናጠቅ አንበሳ አንድ ሆነው ተማማሉ፤ ነፍሶችን በልተዋል፥ ብልጥግናና ሀብትን ወስደዋል፥ በውስጥዋም መበለቶችን አብዝተዋል። |
| 26. | ካህናቶችዋም ሕጌን በድለዋል ቅድሳቴንም አርክሰዋል፤ ቅዱስ በሆነና ቅዱስ ባልሆነ መካከልም አልለዩም፥ በንጹሕና በርኩስ መካከል ያለውን ልዩነት አላስታወቁም፤ ዓይናቸውንም ከሰንበታቴ ሰወሩ እኔም በመካከላቸው ረከስሁ። |
| 27. | በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኵላዎች ናቸው። |
| 28. | እግዚአብሔርም ሳይናገር ነቢያቶችዋ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ከንቱን ራእይ በማየት የሐሰትንም ምዋርት ለእነርሱ በማምዋረት ያለ ገለባ በጭቃ ይመርጓቸዋል። |
| 29. | የምድርን ሕዝብ ግፍ አደረጉ ቅሚያም ሠሩ፤ ድሆችንና ችግረኞችን አስጨነቁ፥ መጻተኛውንም በደሉ። |
| 30. | ቅጥርን የሚጠግንን፥ ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው በመካከላቸው ፈለግሁ፥ ነገር ግን አላገኘሁም። |
| 31. | ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
| ← Ezekiel (22/48) → |