← Ezekiel (17/48) → |
1. | የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
2. | የሰው ልጅ ሆይ፥ በእንቈቅልሽ አጫውት ለእስራኤልም ቤት ምሳሌ ንገር፥ እንዲህም በል። |
3. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ታላቅ ክንፍ ረጅምም ማርገብገቢያ ያለው ላባም የተሞላ፥ መልከ ዝንጕርጕር ታላቅ ንስር ወደ ሊባኖስ መጣ፥ የዝግባንም ጫፍ ወሰደ። |
4. | ቀንበጡንም ቀነጠበ ወደ ከነዓንም ምድር ወሰደው በነጋዶችም ከተማ አኖረው። |
5. | ከምድርም ዘር ወሰደ በፍሬያማ እርሻ ተከለው በብዙም ውኃ አጠገብ እንደ አኻያ ዛፍ አኖረው። |
6. | በበቀለም ጊዜ ቁመቱ ያጠረ አረጉም ወደ እርሱ የሚመለስ ሥሩም በበታቹ የነበረ ሰፊ ወይን ሆነ፥ እንዲሁ ወይን ሆነ አረግም ሰደደ ቀንበጥም አወጣ። |
7. | ታላቅ ክንፍና ብዙ ላባም ያለው ሌላ ታላቅ ንስር ነበረ፤ እነሆም፥ ያጠጣው ዘንድ ይህ ወይን ሥሩን ወደ እርሱ አዘነበለ አረጉንም ከተተከለበት ከመደቡ ወደ እርሱ ሰደደ። |
8. | አረግም ያወጣ ፍሬም ያፈራ የከበረም ወይን ይሆን ዘንድ በመልካም መሬት ውስጥ በብዙም ውኃ አጠገብ ተተክሎ ነበር። |
9. | እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በውኑ ይከናወንለት ይሆንን? ይደርቅስ ዘንድ፥ አዲስ የበቀለውስ ቅጠሉ ይጠወልግ ዘንድ ሥሩን አይነቅለውምን? ፍሬውንስ አይለቅመውምን? ሥሩም የተነቀለው በብርቱ ክንድና በብዙ ሕዝብ አይደለም። |
10. | ተተክሎስ፥ እነሆ፥ ይከናወንለት ይሆንን? የምሥራቅ ነፋስ ባገኘው ጊዜ ፈጽሞ አይደርቅምን? በተተከለበት መደብ ላይ ይደርቃል። |
11. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
12. | ለዓመፀኛ ቤት። ይህ ትርጓሜ ምን እንደ ሆነ አታውቁምን? በላቸው። እንዲህም ብለህ ንገራቸው። እነሆ፥ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ ንጉሥዋንና መኳንንቶችዋንም ማረከ፥ ወደ እርሱም ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። |
13. | ከመንግሥትም ዘር ወስዶ ቃል ኪዳን ከእርሱ ጋር አደረገ፤ አማለውም፥ የምድሪቱንም ኃያላን ወሰደ፤ |
14. | ይኸውም ቃል ኪዳኑን በመጠበቅ እንድትጸና እንጂ መንግሥቱ እንድትዋረድና ከፍ እንዳትል ነው። |
15. | እርሱ ግን በእርሱ ላይ ሸፈተ ፈረሶችንና ብዙንም ሕዝብ ይሰጡት ዘንድ መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ላከ። በውኑ ይከናወንለት ይሆንን? ይህንስ ያደረገ ያመልጣልን? ቃል ኪዳንንስ አፍርሶ ያመልጣልን? |
16. | እኔ ሕያው ነኝና ያነገሠውና መሐላውን የናቀበቱ፥ ቃል ኪዳኑንም ያፈረሰበቱ ንጉሥ በሚኖርበት ስፍራ ከእርሱ ጋር በባቢሎን መካከል በእርግጥ ይሞታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
17. | ብዙዎችን ነፍሳት ለማስወገድ አፈርን በደለደሉ ምሽግም በሠሩ ጊዜ፥ ፈርዖን ከብዙ ሠራዊቱና ከታላቁ ጉባኤው ጋር በሰልፍ አይረዳውም። |
18. | ቃል ኪዳኑንም በማፍረስ መሐላውን ንቆአል፤ እነሆም፥ እጁን ሰጠ፥ ይህንም ሁሉ አድርጎአል፤ ስለዚህ አያመልጥም። |
19. | ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና የናቀውን መሐላዬን ያፈረሰውንም ቃል ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ። |
20. | መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ በወጥመድም ይያዛል፥ ወደ ባቢሎንም አመጣዋለሁ በእኔም ላይ ስላደረገው ዓመፅ በዚያ ከእርሱ ጋር እፋረዳለሁ። |
21. | ጭፍሮቹም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ የቀሩትም ሁሉ ወደ እየነፋሳቱ ይበተናሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ ታውቃላችሁ። |
22. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከረጅሙ ዝግባ ጫፍ ላይ ቀንበጥን ወስጄ አኖረዋለሁ፤ ከጫፎቹ አንዱን ቀንበጥ እቀነጥበዋለሁ፤ በረጅምና በታላቅ ተራራም ላይ እተክለዋለሁ። |
23. | ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፥ ቅርንጫፎችም ያወጣል ፍሬም ያፈራል የከበረም ዝግባ ይሆናል፤ በበታቹም ወፎች ሁሉ ያርፋሉ፥ በቅርንጫፎቹም ጥላ በክንፍ የሚበርር ሁሉ ይጠጋል። |
24. | የዱር ዛፎች ሁሉ ረጅሙን ዛፍ ዝቅ ያደረግሁ፥ አጭሩንም ዛፍ ከፍ ያደረግሁ፥ የለመለመውንም ዛፍ ያደረቅሁ፥ የደረቀውንም ዛፍ ያለመለምሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ እኔም አድርጌአለሁ። |
← Ezekiel (17/48) → |