← Ezekiel (16/48) → |
1. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
2. | የሰው ልጅ ሆይ፥ ለኢየሩሳሌም ርኵሰትዋን አስታውቃት፥ |
3. | እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይላል። ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፤ አባትሽ አሞራዊ ነበረ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች። |
4. | በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልተቈረጠም ንጹሕም ትሆኚ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፥ በጨውም አልተቀባሽም በጨርቅም አልተጠቀለልሽም። |
5. | በተወለድሽበት ቀን ከሰውነትሽ ጕስቍልና የተነሣ በሜዳ ላይ ተጣልሽ እንጂ ከዚህ አንዳች ይደረግልሽ ዘንድ ዓይን አልራራልሽም፥ ማንም አላዘነልሽም። |
6. | በአንቺም ዘንድ ባለፍሁ ጊዜ በደምሽም ውስጥ ተለውሰሽ ባየሁሽ ጊዜ። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ፤ አዎን። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ። |
7. | በእርሻ ላይ እንዳለ ቡቃያ አበዛሁሽ፥ አንቺም አደግሽ ታላቅም ሆንሽ፥ በእጅጉም አጌጥሽ፤ ጡቶችሽም አጐጠጐጡ ጠጕርሽም አደገ፥ ነገር ግን ዕርቃንሽን ሆንሽ፥ ተራቍተሽም ነበርሽ። |
8. | በአንቺ ዘንድ ባለፍሁና ባየሁሽ ጊዜ፥ እነሆ፥ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበረ፤ እኔም መጐናጸፊያዬን በላይሽ ዘረጋሁ ኀፍረተ ሥጋሽንም ከደንሁ፤ ማልሁልሽም ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ አንቺም ለእኔ ሆንሽ። |
9. | በውኃም አጠብሁሽ ከደምሽም አጠራሁሽ በዘይትም ቀባሁሽ። |
10. | ወርቀ ዘቦም አለበስሁሽ በአቆስጣ ቁርበትም ጫማ አደረግሁልሽ፤ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ በሐርም ከደንሁሽ። |
11. | በጌጥም አስጌጥሁሽ በእጅሽም ላይ አንባር በአንገትሽም ላይ ድሪ አደረግሁልሽ። |
12. | በአፍንጫሽም ቀለበት በጆሮሽም ጕትቻ በራስሽም ላይ የክብር አክሊል አደረግሁ። |
13. | በወርቅና በብር አጌጥሽ፥ ልብስሽም ጥሩ በፍታና ሐር ወርቀ ዘቦም ነበረ፤ አንቺም መልካምን ዱቄትና ማርን ዘይትንም በላሽ፤ እጅግ በጣም ውብ ሆንሽ ለመንግሥትም ደረስሽ። |
14. | ባንቺ ላይ ካኖርኋት ከክብሬ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ወጣ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
15. | ነገር ግን በውበትሽ ታምነሻል ስለ ዝናሽም አመንዝረሻል ምንዝርናሽንም ከመንገድ አላፊ ሁሉ ጋር አበዛሽ። |
16. | ከልብስሽም ወስደሽ በኮረብቶች ላይ በዝንጕርጕር ልብስ ያስጌጥሻቸውን መስገጆች ለራስሽ ሠራሽ በዚያም ገለሞትሽ፤ እንዲህም ያለ ነገር ከአሁን በፊት አልነበረም፥ ከእንግዲህም ወዲያ አይሆንም። |
17. | ከሰጠሁሽም ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የክብርሽን ዕቃ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ አድርገሻል አመንዝረሽባቸውማል። |
18. | ወርቀዘቦውን ልብስሽንም ወስደሽ ደረብሽላቸው፥ ዘይቴንና ዕጣኔንም በፊታቸው አኖርሽ። |
19. | የሰጠሁሽንም እንጀራዬን ያበላሁሽንም መልካሙን ዱቄትና ዘይቱን ማሩንም ጣፋጭ ሽታ አድርገሽ በፊታቸው አኖርሽ፥ እንዲሁም ሆኖአል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
20. | ለእኔም የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ወስደሽ መብል ይሆኑ ዘንድ ሠዋሽላቸው። |
21. | ልጆቼን አረድሽ፤ ለእነርሱም በእሳት በኩል አሳልፈሽ ሰጠሽ፤ በውኑ ግልሙትናሽ ጥቂት ነውን? |
22. | በርኵስነትሽና በግልሙትናሽ ሁሉ ዕርቃንሽን ሆነሽ ተራቍተሽም ሳለሽ በደምሽም ተለውሰሽ ሳለሽ የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽም። |
23. | ወዮ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ |
24. | ከክፋትሽም ሁሉ በኋላ የምንዝርናን ስፍራ፥ በየአደባባዩም ከፍ ያለ ቦታን ለራስሽ ሠራሽ። |
25. | በየመንገዱ ራስ ከፍ ያለውን ቦታሽን ሠራሽ፥ ውበትሽንም አረከስሽ፥ ለመንገድ አላፊም ሁሉ እግርሽን ገለጥሽ ግልሙትናሽንም አበዛሽ። |
26. | ሥጋቸውም ከወፈረ ከጐረቤቶችሽ ከግብጻውያን ጋር አመነዘርሽ፥ እኔንም ታስቈጭ ዘንድ ግልሙትናሽን አበዛሽ። |
27. | ስለዚህ፥ እነሆ፥ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቻለሁ ድርጐሽንም አጕድያለሁ፤ ለሚጠሉሽም ከክፉ መንገድሽ የተነሣ ለሚያፍሩ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች ፈቃድ አሳልፌ ሰጥቼሻለሁ። |
28. | አልጠገብሽምና ከአሦራውያን ጋር ደግሞ ገለሞትሽ ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም። |
29. | እስከ ነጋዴዎች ምድር እስከ ከላውዴዎን ድረስ ግልሙትናሽን አበዛሽ። ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም። |
30. | የማታፍረውን የጋለሞታን ሥራ ሁሉ ሠርተሻልና ልብሽ ምንኛ ደካማ ነው? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
31. | በየመንገዱ ራስ የምንዝርናሽን ስፍራ ሠርተሻል በየአደባባዩም ከፍ ያለውን ቦታሽን አድርገሻል። ዋጋዋን እንደምትንቅ እንደ ጋለሞታ አልሆንሽም። |
32. | በባልዋ ፋንታ ሌሎችን ተቀብላ የምታመነዝር ሴትን ትመስያለሽ። |
33. | ለጋለሞቶች ሁሉ ዋጋ ይሰጡአቸዋል፤ አንቺ ግን ለውሽሞችሽ ሁሉ ዋጋ ትሰጫለሽ፥ ከአንቺም ጋር ለማመንዘር በዙሪያሽ ይገቡብሽ ዘንድ መማለጃ ትሰጫቸዋለሽ። |
34. | ግልሙትናሽ ከሌሎች ሴቶች ግልብጥ ነው፤ ማንም ለግልሙትና የሚከተልሽ የለም፤ ዋጋ ሳይሰጥሽ አንቺ ዋጋ በመስጠትሽ በዚህ ነገር ልዩ ሆነሻል። |
35. | ስለዚህ፥ ጋለሞታ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ። |
36. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከውሽሞችሽ ጋር ባደረግሽው በግልሙትናሽ ርኵሰትሽ ስለ ፈሰሰ ኀፍረተ ሥጋሽም ስለ ተገለጠ፥ ስለ ርኵሰትሽም ጣዖታት ሁሉ ስለ ሰጠሻቸውም ስለ ልጆች ደም፥ |
37. | ስለዚህ፥ እነሆ፥ ከእነርሱ ጋር ደስ ያለሽን የወደድሻቸውንም ውሽሞችሽ ሁሉ ከጠላሻቸው ሁሉ ጋር እሰበስባቸዋለሁ፤ በአንቺ ላይ በዙሪያሽ እሰበስባቸዋለሁ፥ ኀፍረተ ሥጋሽንም ሁሉ እንዲያዩ በፊታቸው ኀፍረተ ሥጋሽን እገልጣለሁ። |
38. | በአመንዝሮችና በደም አፍሳሾች ላይ የሚፈረደውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፥ የመዓትንና የቅንዓትን ደምም አመጣብሻለሁ። |
39. | በእጃቸውም አሳልፌ እሰጥሻለሁ፥ የምንዝርናሽንም ስፍራ ያፈርሳሉ ከፍ ያለውንም ቦታሽን ይገለብጣሉ፤ ልብስሽንም ይገፉሻል የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ፥ ዕርቃንሽን አድርገው ዕራቁትሽን ይተዉሻል። |
40. | ጉባኤን ያመጡብሻል በድንጋይም ይወግሩሻል፥ በሰይፋቸውም ይወጉሻል። |
41. | ቤቶችሽንም በእሳት ያቃጥላሉ በብዙም ሴቶች ፊት በላይሽ ፍርድን ያደርጉብሻል፤ ግልሙትናሽንም አስተውሻለሁ፥ እንግዲህስ ዋጋ አትሰጭም። |
42. | መዓቴንም በአንቺ ላይ እጨርሳለሁ ቅንዓቴም ከአንቺ ይርቃል፥ እኔም ዝም እላለሁ ደግሞም አልቈጣም። |
43. | የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽምና፥ በዚህም ነገር ሁሉ አስቈጥተሽኛልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ እኔ ደግሞ መንገድሽን በራስሽ ላይ አመጣለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ሌላንም ነውር በርኵሰትሽ ሁሉ ላይ አትጨምሪም። |
44. | እነሆ፥ በምሳሌ የሚናገር ሁሉ። እንደ እናቲቱ እንዲሁ ሴት ልጂቱ ናት እያለ ምሳሌ ይመስልብሻል። |
45. | አንቺ ባልዋንና ልጆችዋን የጠላሽ የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ አንቺም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የጠሉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ፤ እናታችሁ ኬጢያዊት ነበረች አባታችሁም አሞራዊ ነበረ። |
46. | ታላቂቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ግራሽ የምትቀመጥ ሰማርያ ናት፤ ታናሺቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ቀኝሽ የምትቀመጥ ሰዶም ናት። |
47. | አንቺ ግን በመንገዳቸው አልሄድሽም እንደ ርኵሰታቸውም አላደረግሽም ያው ለአንቺ ጥቂት ነበረና በመንገድሽ ሁሉ ከእነርሱ የሚከፋ ርኵሰት አደረግሽ። |
48. | እኔ ሕያው ነኝና አንቺና ሴቶች ልጆችሽ እንዳደረጋችሁት እንዲሁ ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ አላደረጉም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
49. | እነሆ፥ የእኅትሽ የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ፤ ትዕቢት እንጀራን መጥገብ መዝለልና ሥራ መፍታት በእርስዋና በሴቶች ልጆችዋ ነበረ፥ የችግረኛውንና የድሀውንም እጅ አላጸናችም። |
50. | ኰርተው ነበር በፊቴም ርኩስ ነገር አደረጉ፤ ስለዚህ ባየሁ ጊዜ አጠፋኋቸው። |
51. | ሰማርያም የኃጢአትሽን እኵሌታ አልሠራችም፤ አንቺ ግን ከእኅቶችሽ ይልቅ ርኵሰትሽን አበዛሽ፥ በሥራሽም ርኵሰት ሁሉ አጸደቅሻቸው። |
52. | አሁንም ለእኅቶችሽ ስለ ፈረድሽ እፍረትሽን ተሸከሚ፤ ከእነርሱ የባሰ ኃጢአት ሠርተሻልና ከአንቺ ይልቅ ጻድቃን ናቸው፤ እኅቶችሽንም ስለ አጸደቅሻቸው እፈሪ እፍረትሽንም ተሸከሚ። |
53. | ምርኮአቸውን፥ የሰዶምና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ የሰማርያንና የሴቶች ልጆችዋንም ምርኮ፥ በመካከላቸውም ያሉትን የምርኮኞችሽን ምርኮ እመልሳለሁ፤ |
54. | ስለ አጽናናሻቸው፥ እፍረትን ትሸከሚ ዘንድ ስለ አደረግሽውም ሁሉ ታፍሪ ዘንድ። |
55. | እኅቶችሽም ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ ሰማርያና ሴቶች ልጆችዋም ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ አንቺና ሴቶች ልጆችሽም ወደ ቀድሞ ሁኔታችሁ ትመለሳላችሁ። |
56. | ክፋትሽ ሳይገለጥ በትዕቢትሽ ቀን እኅትሽ ሰዶም በአፍሽ መተረቻ አልነበረችምን? |
57. | አሁን ለሶርያ ሴቶች ልጆችና ለጎረቤቶችዋ ሁሉ፥ በዙሪያሽም ለሚንቁሽ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች እንደ እርስዋ መሰደቢያ ሆነሻል። |
58. | ምንዝርነትሽንና ርኵስነትሽን ተሸክመሻል፥ ይላል እግዚአብሔር። |
59. | ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። አንቺ ቃል ኪዳንን በማፍረስ መሐላን የናቅሽ ሆይ፥ አንቺ እንዳደረግሽ እኔ ደግሞ አደርግብሻለሁ። |
60. | ነገር ግን በሕፃንነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ የዘላለምንም ቃል ኪዳን አጸናልሻለሁ። |
61. | እኅቶችሽንም ታላቂቱንና ታናሺቱን በተቀበልሽ ጊዜ መንገድሽን ታስቢያለሽ ታፍሪማለሽ፤ ለአንቺም ልጆች ይሆኑ ዘንድ እሰጣቸዋለሁ፥ ስለ ቃል ኪዳንሽ ግን አይደለም። |
63. | ስላደረግሽውም ሁሉ ይቅር ባልሁሽ ጊዜ፥ ታስቢ ዘንድ ታፍሪም ዘንድ ስለ እፍረትሽም ደግሞ አፍሽን እንዳትከፍቺ፥ ቃል ኪዳኔን ከአንቺ ጋር አጸናለሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
← Ezekiel (16/48) → |