Ezekiel (15/48)  

1. የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2. የሰው ልጅ ሆይ፥ የወይን ግንድ፥ በዱር ዛፎች መካከል ያለ የወይን አረግ፥ ከዛፍ ሁሉ ይልቅ ብልጫው ምንድር ነው?
3. በውኑ ሥራ የሚሠራበትን እንጨት ከእርሱ ይወስዳሉን? ወይስ ሰዎች ዕቃ የሚንጠለጠልበትን ኵላብ ከእርሱ ይወስዳሉን?
4. እነሆ፥ ለመቃጠል በእሳት ላይ ተጥሎአል፥ እሳቱም ሁለቱን ጫፎቹን በልቶአል፥ መካከሉም ተቃጥሎአል፤ በውኑ ለሥራ ይጠቅማልን?
5. እነሆ፥ ደህና ሳለ ለሥራ ካልጠቀመ፥ ይልቁንስ እሳት ከበላው እርሱም ከተቃጠለ በኋላ እንዴት ሥራ ይሠራበታል?
6. ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዱር ዛፎች መካከል ያለውን የወይን ግንድ እሳት ይበላው ዘንድ እንደ ሰጠሁት፥ እንዲሁ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳልፌ እሰጣለሁ።
7. ፊቴንም በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ከእሳትም ይወጣሉ፥ እሳት ግን ይበላቸዋል፤ ፊቴንም በእነርሱ ላይ ባደረግሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
8. ዓመፅን አድርገዋልና ምድሪቱን ባድማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

  Ezekiel (15/48)