Ezekiel (13/48)  

1. የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2. የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት በሚናገሩ በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፥ ከገዛ ልባቸውም ትንቢት የሚናገሩትን። የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በላቸው፤
3. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ምንምን ሳያዩ የገዛ መንፈሳቸውን ለሚከተሉ ለሰነፎች ነቢያት ወዮላቸው!
4. እስራኤል ሆይ፥ ነቢያትህ በምድረ በዳ እንደሚኖሩ ቀበሮች ናቸው።
5. ወደ ተሰበረው ቅጥር አልወጣችሁም፥ በእግዚአብሔርም ቀን በሰልፍ ትቆሙ ዘንድ ለእስራኤል ቤት ቅጥር አልሠራችሁም።
6. እግዚአብሔር ሳይልካቸው። እግዚአብሔር ይላል የሚሉ ሰዎች ከንቱ ነገርንና ውሸተኛ ምዋርትን አይተዋል፤ ቃሉም ይጠና ዘንድ ተስፋ አስደርገዋል።
7. እኔም ሳልናገር። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል ስትሉ፥ ከንቱ ራእይን ያያችሁ ውሸተኛንም ምዋርት የተናገራችሁ አይደላችሁምን?
8. ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከንቱ ነገርን ስለ ተናገራችሁ ውሸተኛ ራእይንም ስላያችሁ፥ ስለዚህ፥ እነሆ፥ እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
9. እጄም ከንቱ ራእይን በሚያዩ፥ በውሸትም በሚያምዋርቱ ነቢያት ላይ ትሆናለች፤ እነርሱም በሕዝቤ ማኅበር ውስጥ አይገኙም፥ በእስራኤልም ቤት መጽሐፍ አይጻፉም፥ ወደ እስራኤልም ምድር አይገቡም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
10. ሰላም ሳይኖር። ሰላም እያሉ ሕዝቤን አታልለዋልና፤ አንዱም ሰው ቅጥር ሲሠራ፥ እነሆ፥ ገለባ በሌለበት ጭቃ ይመርጉታልና
11. ገለባ በሌለበት ጭቃ ለሚመርጉት ሰዎች። ይወድቃል በላቸው። የሚያሰጥም ዝናብ ይዘንባል፥ ታላቅም የበረዶ ድንጋይ ይወድቃል፥ ዐውሎ ነፋስም ይሰነጣጥቀዋል።
12. እነሆ፥ ግንቡ በወደቀ ጊዜ። የመረጋችሁት ጭቃ ወዴት አለ? አይሉአችሁምን?
13. ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመዓቴ በዐውሎ ነፋስ እሰነጣጥቀዋለሁ፥ ያጠፋውም ዘንድ በቍጣዬ የሚያሰጥም ዝናብ፥ በመዓቴም ታላቅ የበረዶ ድንጋይ ይወርዳል።
14. ገለባም በሌለበት ጭቃ የመረጋችሁትን ቅጥር አፈርሳለሁ ወደ ምድርም እጥለዋለሁ፥ መሠረቱም ይታያል። እርሱም ይናዳል በመካከሉም ትጠፋላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
15. መዓቴንም በግንቡ ላይ ገለባም በሌለበት ጭቃ በመረጉት ላይ እፈጽማለሁ፤ እኔም። ግንቡና መራጊዎቹ የሉም እላችኋለሁ።
16. እነርሱም ስለ ኢየሩሳሌም ትንቢት የሚናገሩ የሰላምን ራእይ የሚያዩላት የእስራኤል ነቢያት ናቸው፥ ሰላምም የለም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
17. አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ከገዛ ልባቸው ትንቢት በሚናገሩ በሕዝብህ ሴቶች ልጆች ላይ ፊትህን አድርግ፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፥
18. እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፍስን ለማጥመድ ለእጅ ድጋፍ ሁሉ መከዳ ለሚሰፉ ለሰውም ሁሉ ራስ እንደ እየቁመቱ ሽፋን ለሚሠሩ ሴቶች ወዮላቸው! የሕዝቤንም ነፍስ ብታጠምዱ በውኑ ነፍሳችሁን ታድናላችሁን?
19. ውሸታችሁን ለሚሰሙት ሕዝቤ እየዋሻችሁ ሞት የማይገባቸውን ነፍሳት ትገድሉ ዘንድ በሕይወትም መኖር የማይገባቸውን ነፍሳት በሕይወት ታኖሩ ዘንድ ስለ ጭብጥ ገብስና ስለ ቍራሽ እንጀራ በሕዝቤ ዘንድ አርክሳችሁኛል።
20. ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እኔ ነፍሳትን እንደ ወፍ በምታጠምዱባት በመከዳችሁ ላይ ነኝ፥ ከክንዳችሁም ወስጄ እቀድዳታለሁ፥ እንደ ወፍም የምታጠምዱአቸውን ነፍሳት እለቅቃለሁ።
21. ሽፋኖቻችሁን ደግሞ እቀድዳለሁ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፥ ከዚያም ወዲያ በእጃችሁ ለመታደን አይሆኑም፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
22. እኔም ያላሳዘንሁትን የጻድቁን ልብ በውሸት አሳዝናችኋልና፥ በሕይወትም ይኖር ዘንድ ከክፉ መንገድ እንዳይመለስ የኃጢአተኛውን እጅ አበርትታችኋልና
23. ስለዚህ ከንቱን ራእይ እንግዲህ አታዩም ምዋርትንም አታምዋርቱም፥ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

  Ezekiel (13/48)