| ← Ezekiel (11/48) → |
| 1. | መንፈስም አነሣኝ፤ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደሚመለከት ወደ እግዚአብሔር ቤትም ወደ ምሥራቁ በር አመጣኝ። እነሆም፥ በበሩ መግቢያ ሀያ አምስት ሰዎች ነበሩ፥ በመካከላቸውም የሕዝቡን አለቆች የዓዙርን ልጅ ያእዛንያንና የበናያስ ልጅ ፈላጥያን አየሁ። |
| 2. | እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ክፋትን የሚያስቡ በዚህችም ከተማ ክፉን ምክር የሚመክሩ ሰዎች ናቸው። |
| 3. | እነርሱም። በውኑ ቤቶችን የምንሠራበት ዘመን የቀረበ አይደለምን? ይህች ከተማ ድስት እኛም ሥጋ ነን ብለዋል። |
| 4. | ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገርባቸው፤ ትንቢት ተናገር። |
| 5. | የእግዚአብሔርም መንፈስ ወደቀብኝ እንዲህም አለኝ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ይህን ነገር ተናግራችኋል፥ እኔም የልባችሁን አሳብ አውቃለሁ። |
| 6. | በዚህች ከተማ ውስጥ ግዳዮቻችሁን አብዝታችኋል በጎዳናዎችዋም ግዳዮችን ሞልታችኋል። |
| 7. | ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመካከልዋ ያኖራችኋቸው ግዳዮቻችሁ እነርሱ ሥጋው ናቸው፥ ይህችም ከተማ ድስቱ ናት፤ እናንተን ግን ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ። |
| 8. | ሰይፍን ፈርታችኋል እኔም ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
| 9. | ከመካከልዋም አወጣችኋለሁ፥ በእንግዶችም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ በላያችሁም ፍርድ አደርጋለሁ። |
| 10. | በሰይፍ ትወድቃላችሁ በእስራኤልም ድንበር እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። |
| 11. | ይህች ከተማ ድስት አትሆንላችሁም እናንተም በመካከልዋ ሥጋ አትሆኑም፥ እኔም በእስራኤል ድንበር እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። |
| 12. | በትእዛዜ አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አላደረጋችሁምና፤ በዙሪያችሁም እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ሕግ አድርጋችኋል። |
| 13. | ትንቢትም በተናገርሁ ጊዜ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፤ እኔም በግምባሬ ተደፍቼ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! በውኑ የእስራኤልን ቅሬታ ፈጽመህ ታጠፋለህን? ብዬ በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ። |
| 14. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
| 15. | የሰው ልጅ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ። ከእግዚአብሔር ዘንድ ራቁ፤ ይህች ምድር ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች የሚሉአቸው ወንድሞችህና ዘመዶችህ የወገኖችህም ሰዎች ሁሉ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ናቸው። |
| 16. | ስለዚህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ወደ አሕዛብ አርቄአቸዋለሁ፥ ወደ አገሮችም በትኛቸዋለሁ፤ ይሁን እንጂ፥ በመጡባቸው አገሮች በእነዚያ ትንሽ መቅደስ እሆናቸዋለሁ በል። |
| 17. | ስለዚህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከአሕዛብ ዘንድ አከማቻችኋለሁ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች እሰበስባችኋለሁ፥ የእስራኤልንም ምድር እሰጣችኋለሁ። |
| 18. | ወደዚያም ይመጣሉ፥ ጸያፉንና ርኩሱንም ነገር ሁሉ ከእርስዋ ያወጣሉ። |
| 20. | በትእዛዜም ይሄዱ ዘንድ ፍርዴንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ እሰጣለሁ፥ ከሥጋቸውም ውስጥ የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። |
| 21. | ልባቸውም ጸያፍንና ርኩስን ነገር በሚከተል በእነርሱ ራስ ላይ መንገዳቸውን እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
| 22. | ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ መንኰራኵሮችም በአጠገባቸው ነበሩ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበረ። |
| 23. | የእግዚአብሔርም ክብር ከከተማይቱ ውስጥ ተነሥቶ በከተማይቱ ምሥራቅ በኩል ባለው ተራራ ላይ ቆመ። |
| 24. | መንፈስም አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም መንፈስ በራእይ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ ምርኮኞቹ አመጣኝ። ያየሁትም ራእይ ከእኔ ወጥቶ ተለየ። |
| 25. | እግዚአብሔርም ያሳየኝን ነገር ሁሉ ለምርኮኞች ተናገርሁ። |
| ← Ezekiel (11/48) → |