| Ezekiel (1/48) → |
| 1. | በሠላሳኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፈቱ፥ የእግዚአብሔርንም ራእይ አየሁ። |
| 2. | ንጉሡ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት |
| 3. | ከወሩም በአምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በከለዳውያን አገር በኮቦር ወንዝ ወደ ቡዝ ልጅ ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ። የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ በእኔ ላይ ሆነች፥ |
| 4. | እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና የሚበርቅም እሳት መጣ፥ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፥ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ እንደሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ ነበረ። |
| 5. | ከመካከልም የአራት እንስሶች አምሳያ ወጣ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፥ ሰውም ይመስሉ ነበር። |
| 6. | ለእያዳንዱም አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት። |
| 7. | እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ እግሮች ነበሩ፤ የእግራቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ እግር ኮቴ ነበረ፤ እንደ ተወለወለ ናስም ይብለጨለጭ ነበር። |
| 8. | በክንፎቻቸውም በታች በእያራቱ ጐድናቸው እንደ ሰው እጅ ነበረ፤ ለአራቱም እንደዚህ ያሉ ፊትና ክንፍ ነበሩአቸው። |
| 9. | ክንፎቻቸው እርስ በእርሱ የተያያዘ ነበረ፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር፥ እያንዳንዱም ፊቱን አቅንቶ ይሄድ ነበር። |
| 10. | የፊታቸው አምሳያ እንደ ሰው ፊት ነበረ፥ ለአራቱም በስተ ቀኛቸው እንደ አንበሳ ፊት፥ በስተ ግራቸውም እንደ ላም ፊት ነበራቸው፥ ለአራቱም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው። |
| 11. | ክንፋቸውም በላይ ተዘርግቶ ነበር፥ የእያንዳንዱም ሁለት ሁለት ክንፋቸው የተያያዙ ነበሩ፥ ሁለት ሁለቱም ገላቸውን ይከድኑ ነበር። |
| 12. | እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፤ መንፈስም ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር። |
| 13. | በእንስሶቹ መካከል እንደሚነድድ የእሳት ፍም ያለ ምስያ ነበረ፤ በእንስሶች መካከል ወዲህና ወዲያ የሚሄድ እንደ ፋና ያለ ምስያ ነበረ፤ ለእሳቱም ፀዳል ነበረው፥ ከእሳቱም መብረቅ ይወጣ ነበር። |
| 14. | እንስሶቹም እንደ መብረቅ ምስያ ይሮጡና ይመለሱ ነበር። |
| 15. | እንስሶችንም ስመለከት፥ እነሆ፥ በአራቱ እንስሶች አጠገብ በምድር ላይ አንድ አንድ መንኰራኵር አየሁ። |
| 16. | የመንኰራኵሩም መልክ እንደ ቢረሌ ነበረ፤ አራቱም አንድ አምሳያ ነበሩ፤ ሥራቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበረ። |
| 17. | በእያራቱ ጐድናቸው ይሄዱ ነበር፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር። |
| 18. | ቁመታቸውም የረዘመና የሚያስፈራ ነበረ፤ የአራቱም ክበብ ዙሪያው በዓይን ተሞልቶ ነበር። |
| 19. | እንስሶቹም በሄዱ ጊዜ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ሄዱ። እንስሶቹም ከምድር ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ መንኰራኵሮቹ ከፍ ከፍ አሉ። |
| 20. | መንፈሱ ወደሚሄድበት ሁሉ እነርሱ ሄዱ፤ የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና መንኰራኵሮቹ በእነርሱ አጠገብ ከፍ ከፍ አሉ። |
| 21. | የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና እነዚያ ሲሄዱ እነዚህ ይሄዱ ነበር፤ እነዚያም ሲቆሙ እነዚህ ይቆሙ ነበር፤ እነዚያም ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር። |
| 22. | ከእንስሶች ራስ በላይ የሚያስፈራ በረዶ የሚመስል የጠፈር አምሳያ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር። |
| 23. | ከጠፈሩም በታች ክንፎቻቸው እርስ በርሳቸው ተቃንተው ነበር፤ ለእያንዳንዱም ገላውን የሚከድኑ ሁለት ሁለት ክንፎች ነበሩት። |
| 24. | ሲሄዱም የክንፎቻቸው ድምፅ እንደ ብዙ ውኃ ድምፅ፥ እንደ ሁሉን የሚችል የአምላክም ድምፅ፥ እንደ ታላቅም ሠራዊት ድምፅ ሆኖ ሰማሁ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር። |
| 25. | በራሳቸውም ላይ ካለው ጠፈር በላይ ድምፅ ተሰማ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር። |
| 26. | በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ። |
| 27. | ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ታች እንደ እሳት ምስያ አየሁ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ። |
| 28. | በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ። |
| Ezekiel (1/48) → |