| ← Exodus (7/40) → |
| 1. | እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል። |
| 2. | ያዘዝሁህን ነገር ሁሉ አንተ ትነግረዋለህ፤ ወንድምህም አሮን የእስራኤልን ልጆች ከአገሩ ይለቅቅ ዘንድ ከፈርዖን ጋር ይናገራል። |
| 3. | እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ በግብፅ ምድርም ድንቄንና ተአምራቴን አበዛለሁ። |
| 4. | ፈርዖንም አይሰማችሁም፥ እጄንም በግብፅ ላይ አደርጋለሁ፥ ሠራዊቴንም የእስራኤልን ልጆች ሕዝቤን በታላቅ ፍርድ ከግብፅ አገር አወጣለሁ። |
| 5. | ግብፃውያንም፥ እጄን በግብፅ ላይ በዘረጋሁ ጊዜ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከመካከላቸው ባወጣሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆነሁ ያውቃሉ። |
| 6. | ሙሴና አሮንም እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ። |
| 7. | ፈርዖንንም በተናገሩት ጊዜ ሙሴ የሰማንያ ዓመት ሰው ነበረ፥ አሮንም የሰማንያ ሦስት ዓመት ሰው ነበረ። |
| 8. | እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ሲል ተናገራቸው። |
| 9. | ፈርዖን። ተአምራትን አሳዩኝ ሲላችሁ፥ አሮንን። በትርህን ወስደህ እባብ እንድትሆን በፈርዖን ፊት ጣላት በለው። |
| 10. | ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ እግዚአብሔርም እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ አሮንም በትሩን በፈርዖንና በባሮቹ ፊት ጣለ፥ እባብም ሆነች። |
| 11. | ፈርዖንም ጠቢባንንና መተተኞችን ጠራ፤ የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ ደግሞ አደረጉ። |
| 12. | እያንዳንዳቸውም በትራቸውን ጣሉ፥ እባቦችም ሆኑ፤ የአሮን በትር ግን በትራቸውን ዋጠች። |
| 13. | እግዚአብሔር እንደ ተናገረ፥ የፈርዖን ልብ ጸና፥ አልሰማቸውምም። |
| 14. | እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። የፈርዖን ልብ ደነደነ፥ ሕዝቡንም ለመልቀቅ እንቢ አለ። |
| 15. | ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነሆ ወደ ውኃ ይወጣል፥ ትገናኘውም ዘንድ አንተ በወንዝ ዳር ትቆማለህ፤ እባብም ሆና የተለወጠችውን በትር በእጅህ ትወስዳለህ። |
| 16. | እንዲህም ትለዋለህ። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር። በምድረ በዳ እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ ብሎ ወደ አንተ ላከኝ፤ እነሆም እስከ ዛሬ አልሰማህም። |
| 17. | እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እነሆ እኔ የወንዙን ውኃ በእጄ ባለችው በትር እመታለሁ፥ ውኃውም ተለውጦ ደም ይሆናል። |
| 18. | በወንዙም ያሉት ዓሦች ይሞታሉ፥ ወንዙም ይገማል፤ ግብፃውያንም የወንዙን ውኃ ለመጠጣት ይጠላሉ። |
| 19. | እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። አሮንን። በትርህን ውሰድ፥ ደምም እንዲሆኑ በግብፅ ውኆች በወንዞቻቸውም በመስኖቻቸውም በኩሬዎቻቸውም በውኃ ማከማቻዎቻቸውም ሁሉ ላይ እጅህን ዘርጋ በለው፤ በግብፅም አገር ሁሉ በእንጨት ዕቃና በድንጋይ ዕቃ ሁሉ ደም ይሆናል። |
| 20. | ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ በትሩንም አነሣ፥ በፈርዖንና በባሪያዎቹም ፊት የወንዙን ውኃ መታ፤ የወንዙም ውኃ ሁሉ ተለውጦ ደም ሆነ። |
| 21. | በወንዙም የነበሩ ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ገማ፥ ግብፃውያንም ከወንዙ ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉም ደሙም በግብፅ አገር ሁሉ ነበረ። |
| 22. | የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ የፈርዖን ልብ ጸና፥ አልሰማቸውምም። |
| 23. | ፈርዖንም ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ፥ ይህንም ደግሞ በልቡ አላኖረውም። |
| 24. | ግብፃውያንም ሁሉ የወንዙን ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉምና በወንዙ አጠገብ ውኃ ሊጠጡ ቆፈሩ። |
| 25. | እግዚአብሔርም ወንዙን ከመታ በኋላ ሰባት ቀን ተፈጸመ። |
| ← Exodus (7/40) → |