| ← Exodus (6/40) → |
| 1. | እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። በጸናች እጅ ይለቅቃችኋልና፥ በጸናችም እጅ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋልና አሁን በፈርዖን የማደርገውን ታያለህ። |
| 2. | እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ |
| 3. | ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር። |
| 4. | የተሰደዱባትንም ምድር፥ የእንግድነታቸውን የከነዓንን ምድር፥ እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን አቆምሁ። |
| 5. | ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ። |
| 6. | ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከግብፃውያንም ባርነት አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፥ |
| 7. | ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። |
| 8. | ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁባት ምድር አገባችኋለሁ፤ እርስዋንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። |
| 9. | ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከሰውነታቸው መጨነቅ ከከባዱም ሥራ የተነሣ ቃሉን አልሰሙትም። |
| 10. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 11. | ግባ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከአገሩ ይለቅቅ ዘንድ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር። |
| 12. | ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት። እነሆ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? ይልቁንም እኔ ከንፈረ ቈላፍ ነኝ ብሎ ተናገረ። |
| 13. | እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ተናገራቸው፥ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንም የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ እንዲያወጣቸው ይነግሩት ዘንድ አዘዛቸው። |
| 14. | የአባታቸውም ቤት አለቆች እነዚህ ናቸው። የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉስ፥ አስሮን፥ ከርሚ፤ እነዚህ የሮቤል ወገኖች ናቸው። |
| 15. | የስምዖንም ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ዶሐር፥ የከነዓናዊቱም ልጅ ሳኡል፤ እነዚህ የስምዖን ወገኖች ናቸው። |
| 16. | እነዚህም እንደ ወገኖቻቸው የሌዊ ልጆች ስሞች ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ ናቸው። የሌዊም የሕይወት ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው። |
| 17. | የጌድሶንም ልጆች እንደ ወገኖቻቸው ሎቤኒ፥ ሰሜኢ ናቸው። |
| 18. | የቀዓትም ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል ናቸው፤ የቀዓትም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነው። |
| 19. | የሜራሪ ልጆች ሞሖሊ፥ ሙሲ ናቸው። እነዚህ እንደ ትውልዳቸው የሌዊ ወገኖች ናቸው። |
| 20. | እንበረምም የአጎቱን ልጅ ዮካብድን አገባ፥ አሮንና ሙሴንም ወለደችለት፤ የእንበረምም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው። |
| 21. | የይስዓር ልጆች ቆሬ፥ ናፌግ፥ ዝክሪ ናቸው። |
| 22. | የዑዝኤል ልጆች ሚሳኤል፥ ኤልዳፋን፥ ሥትሪ ናቸው። |
| 23. | አሮንም የአሚናዳብን የነአሶንን እኅት ኤልሳቤጥን አገባ፥ እርስዋም ናዳብንና አብዮድን አልዓዛርንና ኢታምርን ወለደችለት። |
| 24. | የቆሬ ልጆች አሴር፥ ሕልቃና፥ አብያሳፍ ናቸው፤ እነዚህ የቆሬ ልጆች ወገኖች ናቸው። |
| 25. | የአሮንም ልጅ አልዓዛር ከፉትኤል ልጆች ሚስት አገባ፥ እርስዋም ፊንሐስን ወለደችለት። እነዚህ እንደ ወገኖቻቸው የሌዋውያን አባቶች አለቆች ናቸው። |
| 26. | እነዚህ አሮንና ሙሴ እግዚአብሔር። ከግብፅ ምድር በየሠራዊቶቻቸው የእስራኤልን ልጆች አውጡ ያላቸው ናቸው። |
| 27. | እነዚህ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ያወጡ ዘንድ ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን ጋር የተነጋገሩ ናቸው፤ እነዚህ ሙሴና አሮን ናቸው። |
| 28. | እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ሙሴን በተናገረው ቀን እንዲህ ሆነ፤ |
| 29. | እግዚአብሔር ሙሴን። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እኔ የምነግርህን ሁሉ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር ብሎ ተናገረው። |
| 30. | ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት። እነሆ እኔ ከንፈረ ቈላፍ ነኝ፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? አለ። |
| ← Exodus (6/40) → |