| ← Exodus (5/40) → |
| 1. | ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን መጥተው ፈርዖንን እንዲህ አሉት። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በምድረ በዳ በዓል ያደርግልኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። |
| 2. | ፈርዖንም። ቃሉን እሰማ ዘንድ እስራኤልንስ እለቅቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፥ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም አለ። |
| 3. | እነርሱም። የዕብራውያን አምላክ ተገናኘን፤ ቸነፈር ወይም ሰይፍ እንዳይጥልብን የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንድንሄድ፥ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ እንለምንሃለን አሉት። |
| 4. | የግብፅ ንጉሥም። አንተ ሙሴ አንተም አሮን፥ ሕዝቡን ለምን ሥራቸውን ታስተዋላችሁ? ወደ ተግባራችሁ ሂዱ አላቸው። |
| 5. | ፈርዖንም። እነሆ የምድሩ ሕዝብ አሁን በዝቶአል፥ እናንተም ሥራቸውን ታስፈቱአቸዋላችሁ አለ። |
| 6. | ፈርዖንም በዚያን ቀን የሕዝቡን አስገባሪዎች ሹማምቶቹንም እንዲህ ሲል አዘዘ። |
| 7. | እንደ ወትሮው ለጡብ ሥራ ደግሞ ገለባ ለሕዝቡ አትስጡ፤ ነገር ግን እነርሱ ሄደው ገለባ ይሰብስቡ። |
| 8. | ቀድሞ ያደርጉት የነበረውን የጡብ ቍጥር በእነርሱ ላይ አድርጉት፤ ምንም ከእርሱ አታጕድሉ፤ ሥራ ሰልችተዋልና ስለዚህ። ለአምላካችን እንድንሰዋ እንሂድ እያሉ ይጮኻሉ። |
| 9. | እርሱንም ያደርጉ ዘንድ በሰዎች ላይ ሥራው ይክበድባቸው፤ ከንቱ ቃልም አያስቡ። |
| 10. | የሕዝቡም አስገባሪዎች ሹማምቶቹም ወጡ፥ ሕዝቡንም። ፈርዖን እንዲህ ይላል። ገለባ አልሰጣችሁም። |
| 11. | እናንተ ሂዱ፥ ከምታገኙበትም ስፍራ ገለባ ሰብስቡ፤ ከሥራችሁ ግን ምንም አይጐድልም አሉአቸው። |
| 12. | ሕዝቡም ስለ ገለባ እብቅ ሊሰበስቡ በግብፅ ምድር ሁሉ ተበተኑ። |
| 13. | አስገባሪዎቹም። ገለባ ትቀበሉበት እንደ ነበረ ጊዜ የቀን ሥራችሁን ጨርሱ እያሉ አስቸኰሉአቸው። |
| 14. | የፈርዖንም አስገባሪዎች። ቀድሞ ታደርጉ እንደ ነበራችሁ ትናንትናና ዛሬ የተቈጠረውን ጡብ ስለ ምን አትጨርሱም? እያሉ በእስራኤል ልጆች ላይ የተሾሙትን አለቆቹን ገረፉ። |
| 15. | የእስራኤል ልጆች አለቆችም ወደ ፈርዖን መጡ። ለምን በባሪያዎችህ እንዲህ ታደርጋለህ? |
| 16. | ገለባ አይሰጡንም፥ የጡቡንም ሥራ እንድንሠራ ያዝዙናል፤ እነሆም ባሪያዎችህን ይገርፉናል፤ ግድፈቱ ግን በአንተ ሕዝብ ላይ ነው ብለው ጮኹ። |
| 17. | እርሱ ግን። ሰልችታችኋል፥ ሰልችታችኋል፤ ስለዚህም። እንሂድ ለእግዚአብሔርም እንሠዋ ትላላችሁ። |
| 18. | አሁንም ሂዱ፥ ሥሩ፤ ገለባ አይሰጡአችሁም፥ የጡቡን ቍጥር ግን ታመጣላችሁ አላቸው። |
| 19. | የእስራኤልም ልጆች አለቆች። ዕለት ዕለት ከምትሰሩት ከጡቡ ቍጥር ምንም አታጕድሉ ባሉአቸው ጊዜ ነገሩ እንደ ከፋባቸው አዩ። |
| 20. | ከፈርዖንም ዘንድ ሲወጡ ሙሴንና አሮንን በፊታቸው ቆመው ተገናኙአቸው። |
| 21. | እነርሱም። በፈርዖንና በባሪያዎቹ ፊት ሽታችንን አግምታችሁታልና፥ ይገድሉንም ዘንድ ሰይፍን በእጃቸው ሰጥታችኋቸዋልና እግዚአብሔር ይመልከታችሁ ይፍረድባችሁም አሉአቸው። |
| 22. | ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመለሰና። ጌታ ሆይ፥ ስለ ምን ይህን ሕዝብ አስከፋህ? ስለ ምንስ ላክኸኝ? |
| 23. | በስምህ እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከገባሁ ወዲህ፥ ይህን ሕዝብ አስከፍቶታልና፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አላዳንኸውም አለ። |
| ← Exodus (5/40) → |