| ← Exodus (40/40) |
| 1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። |
| 2. | ከመጀመሪያው ወር በፊተኛው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ማደሪያ ትተክላለህ። |
| 3. | በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፥ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ። |
| 4. | ገበታውንም አግብተህ በእርሱ ላይ የሚኖረውን ዕቃ ታሰናዳለህ፤ መቅረዙንም አግብተህ ቀንዲሎቹን ትለኵሳለህ። |
| 5. | ለዕጣንም የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ታኖራለህ፥ በማደሪያውም ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ትጋርዳለህ። |
| 6. | ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት ታኖረዋለህ። |
| 7. | የመታጠቢያውን ሰንም በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኑረህ ውኃ ትጨምርበታለህ። |
| 8. | በዙሪያውም አደባባዩን ትተክላለህ፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ትዘረጋለህ። |
| 9. | የቅብዓቱንም ዘይት ወስደህ ማደሪያውን በእርሱም ያለውን ሁሉ ትቀባለህ፥ እርሱንም ዕቃውንም ሁሉ ትቀድሳለህ፤ ቅዱስም ይሆናል። |
| 10. | ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ ዕቃውንም ሁሉ ትቀባዋለህ፥ መሠዊያውንም ትቀድሳለህ፤ መሠዊያውም ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናል። |
| 11. | የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውን ቀብተህ ትቀድሳለህ። |
| 12. | አሮንንና ልጆቹንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አቅርበህ በውኃ ታጥባቸዋለህ። |
| 13. | የተቀደሰውንም ልብስ አሮንን ታለብሰዋለህ፤ በክህነትም ያገለግለኝ ዘንድ ቀብተህ ትቀድሰዋለህ። |
| 14. | ልጆቹንም አቅርበህ ሸሚዞችን ታለብሳቸዋለህ፤ |
| 15. | በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አባታቸውን እንደ ቀባህ ትቀባቸዋለህ፤ መቀባታቸውም ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ክህነት ይሆንላቸዋል። |
| 16. | ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ። |
| 17. | እንዲህም ሆነ፤ በሁለተኛው ዓመት በፊተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ማደሪያው ተተከለ። |
| 18. | እግዚአብሔርም እንዳዘዘው ሙሴ ማደሪያውን ተከለ፥ እግሮቹንም አኖረ፥ ሳንቆቹንም አቆመ፥ መወርወሪያዎቹንም አደረገባቸው፥ ምሰሶቹንም አቆመ። |
| 19. | ድንኳኑንም በማደሪያው ላይ ዘረጋ፥ የድንኳኑን መደረቢያ በላዩ አደረገበት። |
| 20. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ጽላቱን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አኖረው፥ መሎጊያዎቹን በታቦቱ ዘንድ አደረገ፥ የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ አኖረው፤ |
| 21. | ታቦቱን ወደ ማደሪያው አገባ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ አድርጎ የምስክሩን ታቦት ሸፈነ። |
| 22. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ገበታውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ ከመጋረጃው ውጭ፥ በማደሪያው በሰሜን በኩል አኖረው፤ |
| 23. | እንጀራውን በላዩ በእግዚአብሔር ፊት አሰናዳ። |
| 24. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው መቅረዙን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በገበታው ፊት ለፊት፥ በማደሪያው በደቡብ በኩል አኖረ፤ |
| 25. | ቀንዲሎቹን በእግዚአብሔር ፊት ለኰሰ። |
| 26. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የወርቁን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በመጋረጃው ፊት አኖረ፤ |
| 27. | የጣፋጩን ሽቱ ዕጣን ዐጠነበት። |
| 28. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በማደሪያው ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ዘረጋ። |
| 29. | ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት አኖረ፥ የሚቃጠለውንና የእህልን መሥዋዕት ሠዋበት። |
| 30. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የመታጠቢያውን ሰን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኖረ፥ ለመታጠቢያም ውኃን ጨመረበት። |
| 31. | በእርሱም ሙሴና አሮን ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ታጠቡ፤ |
| 32. | ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ፥ ወደ መሠዊያውም በቀረቡ ጊዜ ይታጠቡ ነበር። |
| 33. | በማደሪያውና በመሠዊያውም ዙሪያ አደባባዩን ተከለ፤ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ዘረጋ። እንዲሁም ሙሴ ሥራውን ፈጸመ። |
| 34. | ደመናውም የመገናኛውን ድንኳን ከደነ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ሞላ። |
| 35. | ደመናውም በላዩ ስለ ነበረ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም። |
| 36. | ደመናውም ከማደሪያው በተነሣ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በመንገዳቸው ሁሉ ይጓዙ ነበር። |
| 37. | ደመናው ባይነሣ እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። |
| 38. | በመንገዳቸውም ሁሉ በእስራኤል ቤት ሁሉ ፊት የእግዚአብሔር ደመና በማደሪያው ላይ በቀን ነበረና፥ እሳትም በሌሊት በዚያ ላይ ነበረና። |
| ← Exodus (40/40) |